Monday, May 2, 2016

በኢትዮ-ሱማሌ ድንበር በተከሰተ ግጭት ከ10 ሰዎች በላይ ተገደሉ

(ሚያዚያ 24 ፥ 2008)

በቅርቡ በኢትዮጵያና የሶማሊያ የድንበር አካባቢ ከአስር ለሚበልጡ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ግጭት ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት ተወካዮች በጅጅጋ ከተማ በመምከር ላይ መሆናቸው ተገለጠ።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ልዩ ሃይሎች በየጊዜው ከሶማሊያ አርብቶ አደሮች ጋር የሚያደርጉት ግጭት በድንበር ዙሪያ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ስጋት ውስጥ እንዳካተተው የሶማሊያ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የሶማሌ ክልል መስተዳደር ባለስልጣናት በቅርቡ ለተፈጸመው ከ10 በላይ የሶማሊያውያን ግድያ የአል-ሸባብ እጅ አለበት ቢሉም የሃገሪቱ የጋልሙዱግ ግዛት ተወካዮች ግድያውን በታጣቂ ሃይሉ ሳይሆን በኢትዮጵያ ልዩ ሃይሎች መፈፀሙን እንዳስታወቁ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎም የሶማሊያው የጋልሙዱግ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አብደልካሪን ሁሴን ሌሎች የፀጥታ ሃይሎችን በማካተት ከኢትዮጵያ ተወካዮች ጋር እየመከሩ መሆኑም ታውቋል።
በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታም በድንበር ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እልባት ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ ሃላፊው አክለው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በየጊዜው ድንበርን በመጣስ ወደ ሶማሊያ ለመዝለቅ የሚያደርጉት እርምጃ በድንበሩ አካባቢ የጸጥታ ስጋት ፈጥሮ መገኘቱን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮቹን በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር አሰማርቶ ቢገኝም በተለያዩ ጊዜያት የተናጥል ወታደሮችን ወደሶማሊያ በማስረግ ከአልሻባብ ጋር ውጊያን እንደሚያካሄዱም የሶማሊያ ባለስልጣናት ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይሁንና ወታደሮች በድንበር በኩል የሚያደርጉት ጉዞ ከአርብቶ አደሮች ጋር ግጭት ውስጥ እየከተታቸው መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።

No comments:

Post a Comment