Wednesday, May 11, 2016

በባሌ ዞን የጎርፍ አደጋ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2008)

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ለተከታታይ ቀናት የዘነበውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው ጎርፍ፣ ቁጥሩ  ያልታወቀ የሰው ህይወት ማለፉና ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የቀንድ ከብቶች በጎርፉ መወሰዳቸው ተገለጸ ።  በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ኣብርሃም ሃይሌ APA ለተሰኘው የዜና አውታር  ማክሰኞ እንደገለጹት፣ ጎርፉ ቁጥራቸው እስካሁን ያልታወቀ የሰዎችን ህይወት አጥፍቷል፣ በ559 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረውን አዝመራ ሙሉ በሙሉ አውድሟል።

በባሌ ዞን ለቀናት የዘነበውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው ይኸው ጎርፍ፣ ወደጎሮ እና ሶፍ ኡመር ወረዳዎች የሚወስደውን መንገድ ሙሉ በሙሉ በማውደሙ፣ ወደ እነዚሁ ወረዳዎች እና ወደ ዞኑ ይደረግ  የነበረውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ  ቆሟል። ጎርፉ ያጠፋን የሰው ህይወት፣ የእንስሳት፣ የንብረትና፣ የመሰረተልማት መጠን የሚያጠና የቴክኒክ ቡድን በአካባቢው እንደሚሰማራም የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ሃላፊው አቶ አብርሃም ሃይሌ ለዚሁ APA ለተሰኘው የዜና አውታር ገልጸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን ኪንዶ ኮሻ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት በትንሹ 41 ሰዎች መሞታቸውንና በዞኑ በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች የጣለን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋም ወላይታ ከተማን ከዳውሮ ዞን የሚያገናኝ መንገድ ከአገልግሎት ውጭ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።
የባሌ ዞን ብርቅዬ የአገራችን የዱር እንስሳት የሚገኝበት አካባቢ እንደመሆኑ፣ በእንስሳቱ ላይ ምን ያክል ጉዳት እንዳደረሰ የታወቀ ነገር የለም።

No comments:

Post a Comment