Saturday, May 28, 2016

የህወሃት ድል 25ኛው ዓመት ሲከበር

ህወሃት ለንግሥና የበቃበትን 25ኛ ዓመት ለማክበር ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መድቦ ከገጠር ቀበሌ እስከ አገሪቱ ዋና ከተማ ነዋሪ የሆነውን ህዝብ በየሥርቻው ባዘጋጀው የፈንጠዝያ ድንኳን እንዲሰባሰቡለትና በዓሉን እንዲያደምቁለት በተለያዩ መንገዶች ሲያስገድድ ሰንብቶአል። "የግንቦት 20 ድል ባስገኘልን ዕድል ተጠቅመን ለዚህ ወይም ለዚያ ስኬት በቃን" የሚሉ ጥቂቶችን በቴለቪዥንና በሬዲዮ ከማቅረብ አልፎም ለቱባ ቱባ ባለሥልጣናቱና በግል ጥቅም ተጠልፈው በዙሪያው ለተሠለፉ ወፋፍራም ሎሌዎቹ ያሠራውን የኢህአደግ ባንዲራ አልብሶ በትላልቅ አዳራሾች በማጨቅ የ25ቱን አመት ገድል እየሰበከ ጣራው እስኪሰነጠቅ ሲያስጨበጭባቸውም ከርሞአል።
ሁለት ቢሊዮን ብር ማለት 100 /አንድ መቶ/ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማለት ነው። 20/ሃያ/ ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ካላገኘ በቀር ህይወቱ ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ በመስጋት አለም አቀፍ ለጋሽ አገሮች ከግብር ከፋይ ህዝባቸው በሰበሰቡት ገንዘብ የዕርዳታ እህል ሸምተው ለማቅረብ በሚራወጡበት በዚህ የመከራ ሰዓት 100 /አንድ መቶ/ ሚልዮን ዶላር ከመንግሥት ካዝና ወጭ አድርጎ በዓለ ንግሥና ማክበር በአገርና በህዝብ ላይ የሚሠራ ጭካኔ የተሞላበት ከፍተኛ ወንጀል መሆኑ ብዙ አያጠያይቅም። እንዲህ ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል ደግሞ ለህወሃት አዲስ ነገር አይደለም። የዛሬ 25 ዓመት የቤተመንግሥት ሥልጣን ከመቆጣጠሩ ስድስት ዓመት ቀደም ብሎ ተከስቶ በነበረው የ1977 ረሃብ ወቅት እንደቅጠል ይረግፍ ለነበረው የትግራይና የሰሜን ወሎ ህዝብ ከአለም አቀፍ ለጋሾች በሱዳን በኩል የተላከውን የነፍሥ አድን እህል አሳልፎ በመሸጥ አሁን ለድግስ የመደበውን ያህል ገንዘብ ለትጥቅ መሣሪያ መግዣ አውሎታል። በዚያን ወቅት አመራር ላይ የነበሩና በድርጊቱ አዝነው ከድርጅቱ የለቀቁ አባላቱ እንደሚናገሩት በረሃብተኛው ህይወት ተፈርዶ በተገኘ ገንዘብ የተሸመተው የጦር መሣሪያና የሎጄስቲክ መገልገያ ህወሃትን ለድል ለማብቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎአል። በዚህም የተነሳ ረሃብ ህወሃት ለሚያከብረው የግንቦት 20 ድል ባለውለታ ነው። ህወሃት ሥልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ በአገራችን ተከስተው የነበሩ ሌሎች ሁለት የረሃብ አደጋዎችም እንዲሁ ለባለሥልጣናቱ ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ የሆኑበት አጋጣሚዎችን መጥቀስ ይቻላል ። ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ተብሎ በአገሪቱ ሃብት ተገዝቶ የተከማቸን ብዙ ቶን እህል ለጋሽ አገሮች ለተራበው ወገናችን በውጪ ምንዛሪ ገዝተው እንዲያድሉት በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ህወሃቶች ኪስ እንዲገባ ተደርጎአል። ህወሃት 25ኛ የድል አመቱን ሞቅ ደመቅ ባለ አከባበር ለማክበር በዚህን ወቅት ይህንን ያህል ገንዘብ ሲመድብ ለጋሾች ለ20 ሚልዮን ረሃብተኛ ወገናችን ለማቅረብ ከሚሯሯጡት ገንዘብ የሚያገኘውን ወደር የለሽ ትርፍ በሆዱ እያሰላ እንደሆነ መገመት አይስቸግርም ።
የህወሃት ወንጀል በረሃብ በተጠቃው ወገናችን ላይ በተፈጸመው ሰቆቃ ብቻ የሚገለጽ አደለም። ሥልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ ፋሽስት ኢጣሊያ ከፈጸመችው ወንጀል የማይተናነስ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ በበደኖ፤ በአርባጉጉ፤ በወተር፤ በአርሲ፤ በዋካ፤ በጋምቤላ፤ በኦጋዴን፤ በአፋር፤ በአዋሳ፤ በጎንደር፤ በአምቦ፤ በአዲስ አበባና የተለያዩ የአገሪቱ ከተሞችም ፈጽሞአል። ይህ ሁሉ ወንጀል እየተፈጸመብን ላለፉት 25 አመታት ጫንቃችን ላይ ተሸክመነው ለመኖር የተገደድነው የሁላችንም አያት ቅድመ አያቶች ከውጭ ጠላት ተከላክለው ባስረከቡን አገር ላይ እርስ በራሳችን በቋንቋና በሃይማኖት ተከፋፍለን የጎሪጥ እንድንተያይ የተሠራብንን የፖለቲካ ሴራ መሻገር ባለመቻላችን ነው። በዚህም ምክንያት በገዛ ወንድሞቻችን የህይወት መስዋዕትነት ለሥልጣን መብቃታቸውን ዘንግተውት ለሌሎቻችን ያላቸውን ንቀት ለማሳየት እራሳቸውን "ከወርቅ ዘር የተገኘን" እስከማለት ደርሰዋል። በዚህም ዕብሪትና ጥጋብ የአገሪቱን ሃብት በጠራራ ጸሃይ እየዘረፉ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ሥም ሃብት አካብተዋል ፤ አገር ውስጥና ከአገር ውጪ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችንና ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ሆነዋል። በፍትህ እጦት የሚሰቃየው፤ ከቤት ከንብረቱ የተፈናቀለውና ኑሮ የምድር ላይ ሲኦል የሆነበት ሁሉ ከበሮ እየደለቀና የነርሱን የስኬት ድስኩር እየሰማ በየቀበሌው በተጣለው የድግስ ድንኳን እንዲያከብር የተፈለገው የግንቦት 20 በዓል እንግዲህ እነ አዜብ መስፍን፤ ስብሃት ነጋ፤ ሳሞራ ዩኑስ ፤ ስዩም መስፍን፤አቦይ ጸሃዬና ሌሎቹ ቱባ ቱባ የህወሃት ማፊያ መሪዎች የሃብትና የስልጣን ማማ ላይ የተፈናጠጡበትን ቀን ለመዘከር ነው ። ከዚህ በላይ ንቀት ከዚህ በላይ ድፍረት ምን ሊሆን?
አርበኞች ግንቦት 7 ሁለት ቢልዮን ወጪ የወጣበት ይህ 25ኛው የወያኔ የድል ቀን ሲታሰብ፡ በአጋዚ ጦር ልጁን፤ ወንድሙን/እህቱን፤ አባቱን/እናቱን በቅርቡ የተነጠቀው የኦሮሚያ ህዝብ፤ ያለውዴታው በትግራይ ክልል መጠቃለሉን ተቃውሞ ከወያኔ ጋር ትንንቅ ላይ ያለው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ፤ የወያኔን የበላይነት በመቃወማቸው ልጆቹ እስር ቤት የተወረወሩበት ቤተሰብና የእስር ሰለባዎች እንዲሁም የአብራኩ ክፋይ በወጣትነት ዕድሜው ለስደት የተዳረጉበት ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ አንጀቱ በሃዘን እያረረ ይህቺ ቀን ታልፍ ዘንድ አንጋጦ እየጠበቀ እንደሆነ ይገነዘባል።
የወላጅን እንባ ለማበስ፤ የስደትና መከራ ዘመን ፍጻሜ ለማምጣትና በወያኔ ከርሰ መቃብር ላይ የበለጸገች፤ የታፈረችና የተከበረች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋይ አርበኞች በዱር በገደሉ ብቻ ሳይሆን በከተማና በገጠርም ህዝባቸው ውስጥ ተሰማርተዋል።
በወያኔ የ25 አመት ባርነት አገዛዝ የተማረረ ፤ ፍትህ እኩልነትና ነጻነት የጠማው አገር ወዳድ ሁሉ አርበኞች ግንቦት 7 የጀመረውን ሁለገብ ትግል ለማጠናከር ትግላችንን እንዲቀላቀል ወገናዊ ጥሪ ቀርቦለታል።
የተነጠቅነውን የግንቦት7 ድል በትግላችን በማስመለስ ግንቦት 20 የጫነብንን የባርነት ቀንበር እንሰባብራለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

No comments:

Post a Comment