Wednesday, May 4, 2016

የደሴ ነጋዴዎች የሁለት ቀናት የስራ ማቆም አድማ አደረጉ

ሚያዚያ ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የከተማው ወኪላችን እንደገለጸው፣ ሚያዚያ 24 እና 25 ሙሉ በሙሉ፣ ዛሬ ደግሞ በከፊል የገበያ አዳራሾች ተዘግተዋል። በሰላም የገባ የአዳራሽ 624፣ በእድገት የገበያ አዳራሽ 638 ፣ በላኮመዛ የገባያ አዳራሽ 632 እንዲሁም በሚሊኒየም የገበያ አዳራሽ 562 ሱቆች የተዘጉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ከፊሎቹ ዛሬ ስራ ጀምረዋል። የአድማው ምክንያት ከአቅም በላይ የተጣለባቸው ግብርና ካሽ ሬጅስትራር ማሽን እንዲገዙ መገደዳቸው ነው። ነጋዴዎቹ እንደሚሉት በቂ ስራ በሌለበት ሁኔታ፣ ከአቅማቸው ጋር የማይጣጣም ግብር እንዲከፍሉ መገደዳቸው ሳያንስ፣ ትናንሽ የንግድ ድርጅቶች ሳይቀሩ ካሽ ሬጂስትራር ማሽን እንዲገዙ መገደዳቸው አግባብ አይደለም።

ነጋዴዎቹ አድማውን ያደረጉት፣ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ ጠይቀው ከተከለከሉ በሁዋላ ነው። ከአድማው በሁዋላ የንግድ ፈቃዳቸውን ለመመለስ የሄዱ ነጋዴዎች “ የንግድ ፈቃዳችሁን መመለስ ከፈለጋችሁ 20 ሺ ብር ክፈሉ “ መባላቸውን ገልጸዋል። በድርጊቱ የተበሳጩት አንድ ነጋዴ “ከዚህ መንግስት ጋር መነጋገር ለሞተ ሰው መድሃኒት እንደማዘዝ ይቆጠራል” በማለት ብሶታቸውን ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የደሴ ከተማ ከንቲባን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። በሌላ በኩል ከከተማዋ የተውጣጡ በርካታ የኢህአዴግ አባላት ና የመስተዳድሩ ሰራተኞች፣ የመግቢያ ፈተና ውጤት ሳይዙ በደቡብ ወሎ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ተደርጓል። የድርጅት አባሎቹ በትእዛዝ ገብተው እንዲማሩ ከተደረገ በሁዋላ፣ በተማሪዎቹ ላይ የስለላ ስራ እንደሚሰሩም ታውቋል። አባሎቹ በየቀኑ የተማሪዎችን ውሎ ለእለታዊ የመረጃ ልውውጥ አስተባባሪ ሪፖርት እንደሚያደርጉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment