Tuesday, May 31, 2016

ወጣት አቤል በመከላከያ ሰራዊት አባላት ታፍኖ ከተወሰደ ከ4 አመታት በሁዋላ ያላበት አለመታወቁን ዘመዶቹ ተናገሩ

ግንቦት (ሃያ ሦስ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነዋሪነቱ በሃረር ከተማ ሸንኮር ሰፈር የሆነው ወጣት አቤል ሆሶ ሁቤር በመከላከያ ሰራዊት ከእስር ቤት ተወስዶ እስካሁን ድረስ የደረሰበት አልታወቀም።

ከአራት አመታት በፊት በታክሲ ሹፌርነትና በመካኒክነት ሙያ ይተዳደር የነበረው ከኢትዮጵያዊ እናትና ከኩባዊ አባት የተወለደው በቅጽል ስሙ አቤል ኩባ መሰናዶ በሚባለው በሸንኮር ወረዳ በሚገኘው የሰራዊቱ መኖሪያ ውስጥ ይኖር ከነበረ አንድ የመከላከያ ሰራዊት ጋር በመጋጨቱ ወታደሩን በጩቤ ወግቶ እንደ ገደለው ሆን ተብሎ በሀረር ከተማ እንዲወራ በማድረግ ከከተማ እንዲሰወር ተደርጓል።
አቤልን  ከመኖሪያ ቤቱ አግተው በወታደራዊ ካምፕ እስርቤት ውስጥ ከባድ ስቃይ ከፈጸሙበት በኋላ በሀረሪ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ የአስር ዓመት እስራት ተፈረደበት ነበር። ከሁለት ዓመታት እስር በኋላ ሞተ የተባለው ወታደር ሶማሊያ ውስጥ በሰላም አስከባሪነት መሄዱና እዛ መኖሩ በመረጋገጡ በነጻ ከእስር እንዲለቀቅ ተደርጓል።

ወጣት አቤልን ለዚህ ሁሉ ስቃይና እስራት ያበቃው ዋናው ምክንያት “ለአገሩ በነበረው ተቆርቋሪነት ከጦር ሰራዊት ሆስፓታል እያወጡ ለግል ክሊኒኮች የሚሸጡትን የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች፣ መድሀኒቶች ምሰራቅ እዝ በመሄድ በወቅቱ የምስራቅ እዝ አዛዥ ለነበሩት ሜ/ጄነራል ባጫ ደበሌ በመናገሩ ነው”  ይላሉ ቤተሰቦቹ ፡፡በነፃ ከተለቀቀ በኋላም በሙስና የተተበተቡት የሰራዊቱ አባላት አቤልን   በሚዝናናበት፣ በሚሰራበት ቦታዎች እየሄዱ ሲተነኩሱና ሲያስፈራሩት ነበር፡፡
ከእስር ከተፈታ ከስምንት ወራት በኋላ ሸንኮር አካባቢ በሚገኘው ዛቲ ባር ከጓደኛው ጋር በመዝናናት ላይ እያሉ የምስራቅ እዝ አዛዥ የጄነራል አብራሃ ጠባቂ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት፣ በጄነራሉ  ጠባቂ ወታደር ላይ ጉዳት ደርሶበታል ያሉ የሰራዊቱ አባላት መኪና ላይ የተጠመደ መትረየስ በመያዝ የአቤል ሰፈር የሆነውን ሸንኮር ወረዳን ወረሩት።የአካባቢውን ነዋሪዎች በማዋከብ አቤልን እንዲያወጡ ለማድረግ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ይሁን እንጅ በአገር ሽማግሌዎችና በከተማዋ ፓሊሶች ሸምጋይነት አቤል እጁን እንዲሰጥ ተደርጎ የሀረሪ ፓሊስ ኮሚሽን ዋና ግቢ ውስጥ እንዲታሰር ተደረገ።
ከሕግ አግባብ ውጪ ወጣት አቤል በመከላከያዎች ታፍኖ ከሀረሪ ፓሊስ ኮሚሽን ከተወሰደ አራት አመታት ቢያልፉም ወጣቱ  በሕይወት ይኑር አይኑር ዘመዶቹ ለማወቅ አልቻሉም።  የአካባቢው ነዋሪዎችና የአቤል ወላጅ እናት ልጃቸውን አስመልክቶ ለሃረሪ ክልል ፕሬዝዳንት እና ለምስራቅ እዝ አዛዥ  ሜ/ጄነራል አብራሃ  ቢያመለክቱም የልጃቸውን ሁኔታ ማወቅ አልቻሉም። በዚህም የተነሳ ወላጅ እናቱ “ልጄ ሞቶም ከሆነ እርሜን ላውጣ ንገሩኝ” እያሉ እያንዳንዷን ቀን በሰቆቃ ሕይወት ያሳልፋሉ።

No comments:

Post a Comment