Thursday, May 12, 2016

ከእስር በተለቀቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

ግንቦት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክስ ዝርዝሩ እንደሚያሳየው 15 ተማሪዎች ፣ “በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሴኔት ህግ አንቀጽ 177. ቁጥር 2 ንጹስ ቁጥር .15 መሰረት ከሚመለከተው የዩኒቨርስቲው ዲን ፈቃድ ሳያገኙ በቀን 08/04/ 2007 ዓም በግምት ከቀኑ 7 ሰአት ሲሆን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ ካምፓስ ውስጥ በተደረገ ሰልፍ እያወቁ የተካፈሉ በመሆኑ በፈጸሙት የተከለከሉ ስብሰባዎች ላይ መካፈል ወንጀል “ ተከሰዋል።

ተማሪዎቹ “በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የኦሮምያ ተማሪዎች ብቻ እየተገደሉ ነው” የሚል ሃሰተኛ የሆነ እና የህዝብን አስተሳሰብ ሊያናውጥ የሚችል ወሬ በጩከት ያሰሙ በመሆኑ፣ በፈጸሙት የሃሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን ማነሳሳት ወንጀል” ተከሰዋል የሚል በወንጀል ዝርዝር ውስጥ የሰፈረ ሲሆን፣ በተማሪዎች ላይ እንደሚመሰክሩ የተመረጡት ደግሞ ሳጅን አሳየኸኝ ሽፈራው፣ ኮስፐታብል ግምባታው አበራ እና ምክትል ሳጅን ሲማኩ በሽር የተባሉ የፖሊስ ባልደረቦች መሆናቸውን የክሱ ዝርዝር ያመለክታል።
ሁሉም ተማሪዎች ከታህሳስ 10፣ 2008 ዓም ጀምሮ ከእስር የተፈቱ ሲሆን፣ ከአምስት ወራት በሁዋላ ክስ ለመመስረት ለምን እንዳስፈለገ የተገለጸ ነገር የለም።
በኦሮምያ ተነስቶ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ በመልካም አስተዳደርና በስራ አጥነት ችግር የተፈጠረ ነው በማለት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የተናገሩ ቢሆንም፣ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ የኦፌኮ አመራሮች ለተቃውሞው መነሳት ምክንያት ናችሁ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ።

No comments:

Post a Comment