Friday, May 13, 2016

በዛንቢያ 41 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ተፈረደባቸው


ግንቦት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሊዋንጉዋ ማጀስትሬ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በትናንትናው እለት በዋለው ችሎት በሕገወጥ መንገድ ወደ ዛንቢያ ገብተዋል ባላቸው 41 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የፍርድ ውሳኔ አሳልፏል።
ፍርድ ቤቱ የአገሪቱን የሕገወጥ ስደተኞች ሕግ አንቀጽን በመጥቀስ እያንዳንዳቸው ስደተኞች 1 ሽህ 500 የዛንቢያ ክዋቻ እንዲከፍሉ ወይም የሶስት ወራት ጽኑ እስራት ይታሰሩ ዘንድ የፍርድ ብያኔውን ሰጥቷል። በሕገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በዝንባብዌ አድርገው ድንበር አቆራርጠው የሚገቡ ሕገወጥ ስደተኞች ዝውውር ተባብሶ መቀጠሉንና ይህንን ፍልሰት ለመግታት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለማሳለፍ መገደዱን ገልጸዋል። ስደተኞቹ በሚያዙበት ወቅት አንዱ ለማምለጥ ሲሞክር ጉዳት ሲደርስበት ሌላኛው ደግሞ በአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት ጉዳት እንደደረሰበትና ሁለቱም ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በካቶንዲዌይ ሚሽን ሆስፒታል ውስጥ ሕክምናቸው በመከታተል ላይ እንደሚገኙ የድንበር ፓሊስ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል። የዛንቢያ የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊ በበኩላቸው ሕገወጥ ስደተኞችን የሚያዘዋውር አንድ የአገሪቱን ዜጋ መያዛቸውንና የሕገወጥ ስደተኞች ቁጥጥርን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ማስታወቃቸውን ሉሳካ ታይምስ አክሎ አስታውቋል።
በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ ሴንትፍራንሲስ ከተማ የሚገኝ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለ ሱቅ ላይ ጥቃት ተፈጽሞበታል። በቡድን የተደራጁ ዘራፊዎች ኤፍሬም ማዴቦ የተባለ የ27 ዓመት ኢትዮጵያዊን ደብድበው መግደላቸውንና በሌሎች ኢትዮጵያዊና ስደተኞች ሱቆች ላይ ዘረፋ መፈጸሙን የአገሪቱን ፓሊስ ጠቅሶ ግራውንድ አፕ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment