Friday, May 27, 2016

የአቶ አንዳርጋቸው የ9 ዓመት ልጅ በእንግሊዝ መንግስት ላይ ክስ አቀረበች

ግንቦት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአሜሪካና የእንግሊዝ ዜግነትን አጣምራ የያዘችው ምናቤ አንዳርጋቸው የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ በሚከታተሉ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ላይ በጠበቃዎቹዋ አማካኝነት ክስ መስርታለች።

ላለፉት 2 ዓመታት በእስር ላይ የሚገኘው አቶ አንዳርጋቸው ከሁለት አመት በፊት በጣም ለአጭር ጊዜ ካደረገው የስክል ጥሪ በስተቀር ከቤተሰቡ ጋር እንዲገናኝ አልተፈቀደለትም ሲል ጉዳዩን የሚከታተለው ሪፕሪቭ የተባለው የህግ ባለሙያዎች ድርጅት አስታውቋል። አቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ እንዳያገኝና ፍርድ ቤት እንዳይቀርብ መደረጉ ብቻ ሳይሆን፣ የእስር ቤት ባለስልጣናት በእጃቸው እንደሌለ እየገለጹ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።
የተመድ የሰብአዊ መብት ካውንስል፣ የአውሮፓ ፓርላማ እንዲሁም የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት አቶ አንዳርጋቸው እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
ምናቤ አንዳርጋቸው ፣ አባቷ በህገወጥ መንገድ በየመን መንግስት ተላልፎ መሰጠቱን፣ ህገወጥ በሆነ ሁኔታ መታሰሩንና የሞት ፍርድ የተፈረደበት መሆኑን በመግለጽ፣ እንግሊዝ ከዚህ በፊት ለሌሎች ዜጎች ያደረገችውን ጥረት ለአባቷ መፈታት አላደረገችም በማለት ክስ ቅርባለች።
የሪፕሪቭ የሞት ቅጣት ቡድን ዳይሬክተር የሆኑት ማያ ፎአ፣ እንግሊዝ አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ተለቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማድረግ አለባት፣ ዝምታው ማብቃት ይኖርበታል ብለዋል።

No comments:

Post a Comment