Monday, May 30, 2016

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና መውጣቱን ተከትሎ ፈተናው መሰረዙን መንግስት አስታወቀ

ግንቦት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዛሬ ሊካሄድ የነበረው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና መውጣቱን ተከትሎ መንግስት ፈተናውን ለመሰረዝ የተገደደ ሲሆን፣ በተማሪዎች በኩል የተለያዩ አስተያየቶች እየተስተናገዱ ነው። በወላይታ ሶዶ ፈተናው መሰረዙን የሰሙ ተማሪዎች ተቃውሞ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ የፌደራል ፖሊሶች በትነዋቸዋል። ከተለያዩ የገጠር ከተማዎች የመጡ ተማሪዎች፣ ከእንግዲህ ወዲያ ወደ ቤተሰቦቻችን የምንሄድበትም ሆነ ከተማ የምንቆይበት ገንዘብ ስለሌለን መንግስት አንድ ይበለን ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ መንግስት ማትሪክን የሚያክል ፈተና መቆጣጠር አለመቻሉ እየተዳከመ መምጣቱን ያሳያል ይላሉ። ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ ለደረሰባቸው የሞራልና የኢኮኖሚ ኪሳራ የጉዳት ካሳ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
ምንም እንኳን ትምህርት ሚኒስቴር የሰረዘው ወደ ዩኒቨርስቲ የሚያስገባውን የማጠቃለያ ፈተና ቢሆንም፣ ባለፈው ሃሙስ የ10ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተናም እንዲሁ ተሰርቆ መሸጡት ተማሪዎች አክለው ተናግረዋል። ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ተማሪ ጥያቄውንም መልሱንም ከፈተናው በፊት ማግኘቱን ለኢሳት ገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ህዝቡ ተማሪዎችን ሲያጽናና ታይቷል። የ12ኛ ክፍል ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተሰርቆ መውጣቱን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሹጉጤ ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ፈተናው አለመሰረቁን በተናገሩ በሰአታት ውስጥ እንደገና ኮድ 14 የሚባለው የእንግሊዝኛ ፈተና ከነመልሱ መሰረቁን አምነዋል።
ፈተናው መቋረጡ እንደተሰማ በተለይ በቦሌ፣ በ22 እና በካዛንቺስ አካባቢዎች በቡድን የሚጓዙ ተፈታኝ ተማሪዎች ህዝቡ በጋራና በተናጠል እያስቆመ ጭምር ሲያጽናናቸው፣ ሲያበረታታቸው ታይቶአል። ፈተናውን ለመውሰድ ተዘጋጅተው የነበሩት 254ሺ ተማሪዎች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሽፈራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሌላ ፈተና ይዘጋጃል ብለዋል።

No comments:

Post a Comment