Saturday, May 7, 2016

የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ደቡብ ሱዳን መግባታቸው ተነገረ


ኢሳት (ሚያዚያ 28 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከጋምቤላ ክልል ታፍነው የተወሰዱ ከ100 በላይ ህጻናትን ለማስለቀቅ ከቀናት በፊት ወደ ደቡብ ሱዳን ቢገቡም በወታደሮቹ እንቅስቃሴ ዙሪያ በሃገሪቱ ባለስልጣናት ዘንድ አለመግባባ መቀስቀሱ ተገለጸ።
ጥቃቱን ፈጽመዋል የሚባሉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የሚገኙበት የቦማ ግዛት አስተዳደርና የደቡብ ሱዳን መንግስት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ወታደሮች እንቅስቃሴ ዙሪያ ልዩነት መፈጠሩን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘግበዋል።
በሁለቱ አካላት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎም የቦማ ግዛት አስተዳዳሪዎችና የደቡብ ሱዳን መንግስት የየራሳቸውን ተወካዮች ወደ አዲስ አበባ በመላክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተወያዩ መሆኑም ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ዘልቀው ገበተዋል የተባለበት ስፍራና ቁጥራቸው እንኳን በባለስልጣናት በኩል በአግባቡ የማይታወቅ መሆኑም ኳርትዝ አፍሪካ የተሰኘ መጽሄት በዘገባው አስነብቧል።
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ይገኙበታል የሚባለው የቦማ ግዛት ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ግዛቲቱ ዘልቀው ገበተዋል ተብለው ከጁባ መንግስት ቢነገራቸውም ወታደሮቹ የት ስፍራ እንዳሉ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በበኩላቸው የታጣቂ ጎሳ ተወካዮች ታግተው የተወሰዱ ህጻናትን ለመልቀቅ በጎሳ ሽማግሌዎች በኩል ድርድርን እያካሄዱ እንደሆን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከቀና በፊት ወታደሮቹን ወደ ደቡብ ሱዳን ማስገባቱን ቢገልጽም ወታደሮቹ እያደረጉ ስላለው እንቅስቃሴ ግን የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
የደቡብ ሱዳን ፕሪዚደንት ሳል-ባኪር ባለፈው ሳምንት ጎረቤት ሃገራት የተፈጠርውን ችግር በመጠቀም ወደ ሃገሪቱ ዘልቀው ይገባሉ ሲሉ ስጋታቸውን እንደገለፁም መጽሄቱ አውስቷል።
ይሁንና ሃገራቸው እንዲህ ያለን እንቅስቃሴ በቀጣይ ማየት እንደማትሻ ኪር ለሚኒስሮቻቸው በሰጡት መግለጫ መናገራቸውም ታውቋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙት የቦማ ግዛት እና የሃገሪቱ ተወካዮች ወደ ደቡብ ሱዳን ዘልቀው በገቡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ባለስልጣናት ጋር እየመከሩ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።

No comments:

Post a Comment