Monday, September 21, 2015

ዶ/ር አረጋዊ በርኼ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ከህወሃት በተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብላቸውም እንዳማይቀበሉት ገለፁ

የቀድሞው የህወሃት መስራችና በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አባል የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ፣ ህወሃት ኢህአዴግ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞ የሚገኝበት ወቅት በመሆኑ፣ ከድርጅቱ የለቀቁ የቀድሞ አባሎቹን በማነጋገር ወደ ድርጅታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል።
ህወሃት/ኢህአዴግ በራሱ የውስጥ ችግር መዳከሙን የሚገልጹት ዶ/ር አረጋዊ ፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት እርሳቸውም ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በተደጋጋሚ እንዳናገሯቸው ይሁን እንጅ እርሳቸው የሚታገሉለት አላማ ጥሪውን እንዳይቀበሉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

.
ዶ/ር አረጋዊ «በቅርቡ የትህዴን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሞላ አስጎዶም ወደ ህወሃት መመለሳቸው ወይም ሌሎች የቀድሞው ታጋዮች ወደ ድርጅቱ መመለሳቸው ለህወሃት ኢህዴግ ትንሽ ስትንፋስ ይሰጠው ካልሆነ ችግሩን አይቀርፍለትም» ሲሉ ያክላሉ። በእርሳቸውና አቶ ሞላ አስገዶም ይመሩት በነበረው ትህዴን መካከል የቆየ ግንኙነት አለ ወይ ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር አረጋዊ፣ ኮሎኔል ፍሰሃ ድርጅቱን ይመሩ በነበረበት ወቅት ግንኙነት እንደነበራቸው ይሁን እንጅ አቶ ሞላ አመራሩን ከያዙት በኋላ ግንኙነቱን ማቋረጣቸውንና አቶ ሞላ በተደጋጋሚ ሊቀርቧቸው ቢሞክሩም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ገልጸዋል።
.
ዶ/ር አረጋዊ ፣ አቶ ሞላም ሆኑ ሌሎች የህወሃት/ኢህአዴግ አባላት ወደ ድርጅቱ ተመልሰው መግባታቸው የትግራይ ህዝብ ሊወቀስ እንደማይገባው፣ የትግራይን ህዝብ በደፈናው ከህወሃት ጋር ደምሮ ለማየት የሚደረገው ሙከራ ፣ እንደ ህወሃት/ኢህአዴግ ዘረኛ መሆንና በትግራይ ውስጥ ያለውን ብሶት ላለማየት ከመፈለግ የሚመጣ ነው ብለዋል። ዲሞክራሲያዊ መሰረት ያለው ስርዓት ለመገንባት እንታገላለን የሚሉ ሃይሎች የኢህአዴግን አገዛዝ ለማስወገድ መተባባር ይኖርባቸዋል ሲሉም ዶ/ር አረጋዊ ተናግረዋል። ሙሉውን ቃለምልልስ እንደደረሰ እናቀርበዋለን።

No comments:

Post a Comment