Wednesday, September 9, 2015

በአርበኞች ግንቦት7 ስም የተከሰሱት በእስር ቤት የደረሰባቸውን በደል ተናገሩ

ጷግሜን ፬ (አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል የቀድሞው አንድነት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ የነበረው አቶ ተስፋዬ ታሪኩ በእስር ቤት እየደረሰባቸው ያለውን ስቃይ እንዲሁም መስክሮች በሃሰት መስክሩ ተብለው እግራቸው እንደተሰበረ ሲገልጽ፣ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የታች አርማጭሆ ተወካይ አቶ አንጋው ተገኝ ደግሞ በእስር ቤት ውስጥ በጨለማ ቤት በመቀመጡ አይኑን መታተመሙንና ህክምና መከልከሉን ገልጿል። ኢሳት ያናገረው አንደኛው የሃሰት ምስክር ደግሞ “የግዳጅ ስራ ስለሆነ ምንም አማራጭ አልነበረንም” በማለት በጫና ውስጥ ሆኖ መናገሩን ገልጿል።

አቃቤ ህግ በ1ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን፣ በ8ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ታሪኩ፣ በ13ኛ ተከሳሽ እንግዳው ቃኘው፣ በ15ኛ ተከሳሽ አግባው ሰጠኝ ላይ የሰነድ ማስረጃ እንጅ የሰው ምስክር እንደሌለው ገልጾ፣ በ2ኛ ተከሳሽ በላይነህ ሲሳይ፣ 3ኛ ተከሳሽ አለባቸው ማሞ፣ 4ኛ ተከሳሽ አወቀ ሞኝ ሆዴ፣ 5ኛ ተከሳሽ ዘሪሁን በሬ እና በትናንትናው ዕለት ምስክሮች የተሰሙበት 7ኛ ተከሳሽ አማረ መስፍን ላይ ምስክሮቹን ማሰማቱን ነገረ -ኢትዮጵያ ዘግቧል።
“የአቶ አማረ መስፍን ቤት በፖሊስ ተከቦ ሲበረበር የጦር መሳሪያና ሰነዶች ይኖራሉ ተብሎ ለእማኝነት እንደተጠራ የተናገረው 7ኛ ምስክር ፣ ‹‹በአቶ አማረ መስፍን ቤት ይኖራል ተብሎ የተጠበቀው መሳሪያና ሰነድ አልተገኘም፡፡›› ሲል መስክቷል፡፡
“በተከሳሹ የግል ድርጅት በሆነው ሱቅ ውስጥ ሽጉጥ እንደተገኘ የተናገረው ምስክሩ፣ መሳሪያው ህጋዊ ነው ወይስ አይደለም ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹መተማ ውስጥ ሁሉም ሰው የድርጅት መጠበቂያ መሳሪያ አለው፡፡ እኔ በዚሁ ከተማ ስለሆነ የምኖረው አውቀዋለሁ፡፡ መንግስት አስመዝግቡ ብሎ ይመጣል እንጅ ነዋሪው ለድርጅቱ መጠበቂያ ያልተመዘገበም ቢሆን መሳሪያ ይኖረዋል፡፡›› ሲል ያልተጠበቀ ምስክርነት ሰጥቷል።
“በውንብድና ወንጀል ተከሶ 10 አመት ተፈርዶበት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2005 ዓ.ም ታስሮ እንደተፈታ የገለፀው 8ኛ ምስክር” ደግሞ፣ በአቶ በላይነህ ሲሳይ በኩል ስልካቸውን አገኘሁ ያላቸው ሰዎች ኤርትራ ውስጥ የሚኖሩ የአርበኛው ግንባር አመራሮች በኢትዮጵያ የስልክ ቁጥር ሲደውሉለት እንደነበር፣ የአርበኛው ግንባር አመራሮች መሳሪያና ገንዘብ እንዲወስድ ሲጠይቁት ለገንዳውሃ አስተዳደር አመልክቶ መሳሪያውንና ገንዘቡን እንዲቀበል እንዳበረታቱት፣ መልምለውኛል ያላቸውንና ተመልምለዋል ያላቸውን ሰዎች እንቅስቃሴ ለመንግስት ሲያሳውቅ” እንደቆየ ተናግሯል።
በአቶ አለባቸው ማሞ ላይ የመሰከረው 9ኛ ምስክር የኢህአዴግ አባል መሆኑን እንዲሁም በመስቀለኛ ጥያቄ የደህንነት ሰራተኛ መሆኑን አምኗል፡፡ ኤርትራ የነበሩ አመራሮች ‹‹ብአዴን አይቀጥልም፡፡ በመሆኑም ከህዝብ ጋር አትቀያየም፡፡ ክፉ ስራ አትስራ›› እያሉ ሲደወሉለት እንደነበር ገልጾ፣ ተከሳሹ ስልኩን ለግንቦት7 አመራሮች እንደሰጠበት መስክሯል፡፡ 9ኛ ምስክርን ጨምሮ ሌሎችም የአቃቤ ህግ ምስክሮች ፍርድ ቤት በተገኙ የተከሳሾች ቤተሰቦች ማስፈራሪያና ዛቻ እየተፈፀመባቸው ነው ሲል አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረቡን ጋዜጣው ዘግቧል።
አቶ አወቀ ሞኝሆዴ ላይ የመሰከረው 10ኛ ምስክር ወደ ኤርትራ ለመሄድ ማይካድራ ላይ እንደተያዘ ገልጾ፣ ‹‹ማይካድራ ላይ ያዙን፡፡ ሁመራ ወሰዱንና ተገረፍን፡፡›› ብሏል፡፡ በእስር ላይ እንደቆየም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በተመሳሳይ አቶ ዘሪሁን በሬ ላይ የመሰከሩት 12ኛ ምስክርም ‹‹ማይካድራ ላይ ከተያዝኩ በኋላ ሁመራ ላይ ተቀጥቻለሁ፡፡›› ብሎአል።
አቃቤ ህግ በዛሬው ዕለት ሁሉንም ምስክሮች አሰምቼ እጨርሳለሁ ብሎ የነበር ቢሆንም፣ ሁለቱ ምስክሮች መጥሪያው ደርሷቸው ስላልመጡ፣ እንዲሁም አራት ምስክሮች መጥሪያ ስላልደረሰላቸው ረዥም ቀጠሮ እንዲሰጠው ቢጠየቅም ተከሳሾች ተቃውመዋል።
8ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ‹‹ባለፉት 11 ወራት ያለጠያቂ፣ ቤተሰብም እኛም ብዙ ተሰቃይተናል፡፡ በግፍ እየተሰቃየንም እንገኛለን፡፡ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን በታቀደው ጊዜ ማቅረብ አለመቻሉ ደግሞ ከበደላችን በላይ በደል እየተፈፀመብን ነው፡፡ ስቃዩ በእኛ ብቻ ሳይሆን በምስክሮች ላይም ጭምር ነው፡፡ የሀሰት ምስክርነት ስጡ ተብለው ሁለት ሰዎች አካላቸውን አጥተዋል›› ሲል ተናግሯል። ፍርድ ቤቱ የተስፋዬን ንግግር ማስቆሙም ተዘግቧል። 14ኛ ተከሳሽ አቶ አንጋው ተገኝ ደግሞ ‹‹በማዕከላዊ 6 ወር ጨለማ ቤት ስለቆየሁ አይኔን ታምሜያለሁ፡፡ ለአይኔ መነፀር እንደሚያስፈልግ ቢታወቅም ህክምና እንዳላገኝ ተከልክያለሁ፡፡›› በማለት ቅሬታ አቅርቧል።
የተከሳሽ ጠበቃ ‹‹አቃቤ ህግ ችሎቱን እየመራው ነው›› ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት የአቃቤ ህግን ቀሪ 6 ምስክሮች ለመስማት ለህዳር 13/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ኢሳት አንደኛውን የሃሰት ምስክር በስልክ ያናገረው ሲሆን፣ ምስክሩም ” የግዳጅ ስራ ስለሆነ ምንም አማራጭ የለንም፣ የተባልነውን ብቻ ስራ መስራት ነው” የሚል መልስ ሰጥቷል። ዝርዝር መረጃ እንዲሰጥ ሲጠየቅ “እባካችሁ ታስፈጁናላችሁ” በማለት በዝርዝር ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል

No comments:

Post a Comment