Tuesday, September 29, 2015

የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ስጋት ላይ ናቸው

መስከረም ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ መራሹ ገዥው ፓርቲ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን አጋልጡ በሚል ከፍተኛ ግፊት ማድረጉን ተከትሎ ትርምስ መፈጠሩ ተሰማ፡፡

የመገናኛ ብዙሃኑን መሪዎች ጨምሮ አንዳንድ ጋዜጠኞች በሙስናና ብልሹ አሠራር የሚጠረጠሩ መሆናቸው ይበልጥ ነገሩን አወሳስቦታል፡፡
ኢህአዴግ በቅርቡ በመቀሌ ከተማ ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ በመልካም አስተዳደር ችግሮች መተብተቡንና ሕዝቡ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠው በማመን ችግሩን ለመቅረፍ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ነበር፡፡
“ትኩረት መደረግ ያለበት በመልካም አስተዳደር ችግርን ላይ ነው፣ ችግር ፈጣሪዎችን ማጋለጥ አለብን” የሚል መመሪያ ከአለቆቻቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እየሰሙ መሆኑን የሚናገረው አንድ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ ፣ ይህን ዘገባ ሰርተን ችግር ቢገጥመን የተሰጠን ምንም ዓይነት ዋስትና የለም ብሏል፡፡

ቀድሞውንም ለሕዝብ ችግር ትኩረት ስጡ እየተባለ ብዙ ጸረ ሕዝብ የሆኑ ዘገባዎችና ዜናዎች ይሰሩ ነበር ያለው ጋዜጠኛው፣ አሁንም ሙስናና ብልሹ አሰራርን አጋልጡ፣ አትታገሱ በማለትና ጋዜጠኛውን ጭዳ በማድረግ የሚመጣ ለውጥ አለ ብሎ እንደማያምን ጠቅሶአል፡፡
እንደኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከአናቱ ጀምሮ የበሰበሰ ተቋም የለም ያለው ይህ ጋዜጠኛ፣ የእነዚህ ተቋማት አስተዳዳሪዎች መልሰው ሙስናን አጋልጡ፣ መልካም አስተዳደርን ችግርን ተዋጉ በሚል ራሳቸው አዋጊ ሆነው መምጣታቸው የሚገርም ነው ብሎአል፡፡
በአዲስዘመን ጋዜጣም ጋዜጠኞች ደፈር ብላችሁ መንግስትን አትተቹም በሚል ጋዜጠኞች አበሳቸውን እያዩ መሆኑንና በዚህ ምክንያት ስራ የማይሰራበት ደረጃ መደረሱን ተናግሯል።

No comments:

Post a Comment