Wednesday, September 16, 2015

ንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል ለቡ አካባቢ በሚገኝ መዝናኛ ቤት ውስጥ ሰኞ ምሽት አንዲት ወጣት መግደሉ ተሰማ

አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል ለቡ አካባቢ በሚገኝ መዝናኛ ቤት ውስጥ ሰኞ ምሽት አንዲት ወጣት መግደሉ ተሰማ፡፡ ግለሰቡ ራሱን ለማጥፋት ቢሞክርም ተርፎ በሕክምና ላይ ይገኛል፡፡
ሰሎሜ ጉልላት የተባለችው የ20 ዓመት ወጣት ከጓደኛዋ ጋር በመሆን በለቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ በሚገኝ የጓደኛቸው መዝናኛ ውስጥ በመዝናናት ላይ እያሉ ነው ከተጠርጣሪው ገዳይ ጋር የተገናኙት፡፡
ለጊዜው ስሟን መናገር ካልፈለገችው ጓደኛዋ መረዳት እንደተቻለው፣ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰው ግለሰብ ከዚህ ቀደም ሰሎሜን አስቸግሮ ከሚያውቅ ግለሰብ ጋር በሚዝናኑበት ባር ውስጥ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ሁለቱ ሴት ጓደኛሞች መዝናኛ ባሩ ውስጥ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊት፣ ወደ መፀዳጃ ቤት ለመግባት ተስማምተው መሄዳቸውን ታስታውሳለች፡፡ ክፍሉ ራሱን የቻለ መዝጊያ ኖሮት መፀዳጃ ክፍሎቹም ራሳቸውን የቻሉ መሆናቸውን የገለጸችው የዓይን እማኟ፣ አንዱን ክፍል በሚከፍቱበት ወቅት ዩኒፎርም የለበሰው ፖሊስ ውስጥ ሆኖ ስላዩት ይቅርታ መጠየቃቸውን ትገልጻለች፡፡
ይቅርታቸውን ተቀብሎ እንደወጣ እነሱ ወደ መፀዳጃ ክፍሎቹ ገብተው ከደቂቃ በኋላ ሲወጡ የዋና ክፍሉን በር ቆልፎ ፖሊሱ መፀዳጃ ክፍል ውስጥ እንደጠበቃቸው አስረድታለች፡፡ ወደ ሰሎሜ ተጠግቶ ‹‹አንቺ ሰው የማታናግሪው ለምንድነው?›› ብሎ በጥፊ እንደመታትና እንደወደቀች የገለጸችው የሟች ጓደኛ፣ እሷ በሁኔታው ተደናግጣ ወደ መፀዳጃ ክፍሉ ገብታ መቆለፏን ትናገራለች፡፡ በክፍሉ ውስጥ እንዳለች የተኩስ ድምፅ መሰማቱን፣ የማቃሰት ድምፅ ስትሰማ መውጣቷን ገልጻለች፡፡

ጓደኛዋ ሰሎሜም ሆነች ፖሊሱ ወድቀው እንዳየቻቸው ሰው እንዲደርስላት ብትጮህም፣ ለደቂቃዎች ያህል ማንም እንዳልደረሰ ትናገራለች፡፡
በኋላ ከደረሰችላት አንዲት እንስት ጋር በመሆን እስትንፋሷ የነበረውን ጓደኛዋን ለመርዳት እየሞከረች ሳለ፣ ፖሊሶች እንደደረሱና በሥፍራው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ በፒክ አፕ መኪና ይዘዋት መሄዳቸውን፣ ነገር ግን የጓደኛዋ ሕይወት ማለፉን ገልጻለች፡፡
ተጠርጣሪው የፖሊስ ባልደረባ ጭንቅላቱን በጥይት መትቶ ራሱን ለማጥፋት ቢሞክርም ሕይወቱ ባለማለፉ የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገለት ነው፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው ገና በሕክምና ላይ በመሆኑ ፖሊስ ቃሉን እንዳልተቀበለ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የወጣት ሰሎሜ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማክሰኞ መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በለቡ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

No comments:

Post a Comment