Tuesday, June 19, 2018

ለጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ ተዘጋጀ

 (ኢሳት ዜና ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓ/ም) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ለመደገፍና ለማበረታታት የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ይደረጋል። አስተባባሪዎቹ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰልፉ አላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዷቸውን ጅምር የማሻሻያ ሀሳቦች ለመደገፍ፣ለማመስገንና ይበልጥ ለማበረታታት ነው። ከዚህ በተረፈ ሰልፉ የማንንም ፓርቲ አጀንዳ አያስተናግድም ብለዋል ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ጉደታ ገላልቻ። በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ ብቻ በቂ ቢሆንም፣ ለዚህ እጅግ በርካታ የመዲናዋና አጎራባች ነዋሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ለሚጠበቀው ሰልፍ ፈቃድ ለማግኘት ለአዲስ አበባ መስተዳድር ጥያቄ ማቅረባቸውንም አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል። በአቶ ጉደታ ገላልቻ ከሚመራው እና ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጠው የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት መካከል፦ ከዓመታት እስር በኋላ በቅርቡ የተፈታው አቶ አበበ ቀስቶ፣ የአምቦ ዩኒቨርሲቲው መምህር የሆነው አክቲቪስት ስዩም ተሾመ፣ አክቲቪስት ስንታዬሁ ቸኮል እና አቶ አየለ ደጋጋ
ይገኙበታል። ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማውጣት በቅን ልብ ጥረት እያደረገ ያለው መሪ ድጋፍ ያስፈልገዋል ያሉት አስተባባሪዎቹ፣ ሰልፉ ፍቅር የሚወደስበት፣ ስለ አንድነት፣ይቅርታ እና ምህረት የሚዘመርበት ፍጹም ሰላማዊ ሰልፍ ይሆናል ብለዋል። ከዚያም በተጓዳኝ ጅምር ለውጡን ለመቀልበስ ለሚሹ ኃይሎችም- ጠቅላይ ሚኒስትሩን መንካት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የፍጻሜውን ጦርነት ሊያስከትል የሚችል ጸብ ውስጥ መግባት እንደሚሆን ግልጽ እና ጠንካራ መልዕክት ይተላለፍላቸዋል ተብሏል። ሰልፉ፣በዋነኝነት ሕዝቡ ለለውጡ ለሚሠራለት መሪ ምስጋና የሚያቀርብበት መድረክ ነው ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል። ለሰልፉ ድምቀት ለመስጠት ለአስር ሺህ ሰዎች በነጻ ቲሸርት አሳትሞ የሚያከፋል ሰው መገኘቱም አክቲቪስ ስንታዬሁ ቸኮል ገልጿል። በርካታ የደሴ ወጣቶችም ለቅዳሜው ሰልፍ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያመሩ አሳውቀዋል። ይህ_ሰልፍ_በኢትዮጵያ_ታሪክ_መሪን_ለማመስገን_በህዝብ ፍላጎት የተጠራ የመጀመሪያው ሰልፍ እንደሆነም አውስተዋል። እንደ ኮሚቴ አባላቱ መግለጫ ይህ ሰልፍ-ሕዝቡ ቅዳሜ ጠዋት አንድ ሰዓት ጀምሮ ከ100 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ካሉ ከማንኛውም ቦታዎች ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በመትመም የሚያደገው ግዙፍ ሰልፍ ነው። የአዲስ አበባ መግቢያ በሮች ሁሉ በድጋፍ ሰልፉ ለመሳተፍ በማለዳው ከቤታቸው ነቅለው የሚወጡ ሰዎችን ያስተናግዳሉ። በመዲናዋ ይደረግ እንጂ በአጠቃላይ ሰልፉ የመላው ኢትዮጵያዊ ሰልፍ ነው ያሉት አስተባባሪዎቹ፣ “ጅምር ለውጡ በጋራ ይወደሳል፣ ለለውጡ ምክንያት የሆነው ሰው ይመሰገናል” ብለዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ ሕዝባዊ ሰልፍ በሚያዚያ ሰላሳ ቅንጂት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ የጠራውና ዲሞክራሲ የተወደሰበት ግዙፍ ሰልፍ መሆኑ ይታወቃል። ብዙዎች “ሱናሚ” ብለው በሰዬሙት የቅንጅቱ ሰልፍ እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ የመዲናዋና አጎራባች ከተሞች ነዋሪዎች መገኘታቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment