Thursday, June 28, 2018

የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት ከስልጣናቸው ሊነሱ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 21/2010)የደቡብ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ከስልጣናቸው እንደሚነሱ ተገለጸ።
ሰሞኑን የድርጅቱ አመራር ሆነው የተመረጡት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በምትካቸው እንደሚመረጡም ተመልክቷል።
የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ ከሃላፊነታቸው እንደሚነሱና በሌላ የደኢሕዴን አባል እንደሚተኩ የዘገበው በሀገር ቤት የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው።
አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ተክተው ከሐምሌ 6/2005 ጀምሮ ላለፉት 5 አመታት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ደሴ ዳልኬ በአቶ ማቲዎስ እንደሚተኩ ተመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተሰብስቦ ሹም ሽሩን እንደሚያካሂድም ይጠበቃል። አቶ ደሴ ዳልኬን ይተካሉ የተባሉት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ባለፈው ማክሰኞ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳን ተክተው የደኢሕዴን ምክትል ሊቀመንበር የሆኑ ናቸው ።
የዛሬ ሶስት ወር የደኢሕዴን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡትና አቶ ሃይለማርያምን የተኩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስፍራውን ለወጣቶች መልቀቅ ያስፈልጋል በሚል ባለፈው ሰኞ ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት መልቀቃቸው ይታወሳል።
ማክሰኞ እለት ደግሞ ምክትላቸው አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ በተመሳሳይ ተነስተዋል። ሁለቱ ግለሰቦች ከድርጅቱ አመራርነት ቢለቁም በሚኒስትርነት ስልጣናቸው ግን ቀጥለዋል።
አንዳንድ የቅርብ ምንጮች እንደሚገልጹት አቶ ሽፈራው ሽጉጤና አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ለቅልበሳ ከሚንቀሳቀሰው የሕወሃት ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ከተከሰተው ግጭት እንዲሁም በተለያዩ ስፍራዎች እየታየ ያለው ግጭት ለቅልበሳ ከሚንቀሳቀሰው የሕወሃት ቡድን ጋር የተያያዘ መሆኑን ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment