Wednesday, June 27, 2018

ኢ ኤን ኤን ቴሌቪዥን ስርጭቱን ሊያቋርጥ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 20/2010) ኢ ኤን ኤን የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ስርጭቱን ሊያቋርጥ መሆኑ ተሰማ።
በመጪው አርብ 110 የሚሆኑ ቋሚ ሰራተኞቹን በይፋ ሊያሰናብት መዘጋጀቱም ታውቋል። ጣቢያው በሕወሃቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ቦርድ ሰብሳቢነት ሲመራ መቆየቱ ይታወሳል።
የኢ ኤን ኤን ከስርጭት መውጣት ምክንያት የመንግስት መስሪያቤቶች መረጃ ለጣቢያው መስጠት በማቆማቸው መሆኑ ይነገራል።
ለጣቢያው ስፖንሰር የሆኑት ኢትዮ ቴሌኮም እና ንግድ ባንክ በድንገት ውላቸውን ማቋረጣቸው የጣቢያውን ገቢ ማሳጣቱንም የኢ ኤን ኤን ምንጮቻችን ለዋዜማ ጠቁመዋል።

ጣቢያው ከዳሽን ባንክ በብድር ሊያገኝ የነበረው 500 ሚሊየን ብር ብድር በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ እንዲሰረዝ መደረጉም ነው የተገለጸው።
ኢ ኤን ኤን በሃገሪቱ ህዝባዊ ተቃውሞ በተፋፋመበት ወቅት ሁከት አባባሽና “ብሄር ከብሄር ለማጋጨት የሚቀሰቅስ” ዘገባ በማቅረብ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር።
ለዘገባው ሀሰተኛ ምስል መጠቀሙና ዘገባው የተላለፈበት ሰዓት ተዳምረው ጣቢያው “ስውር ተልዕኮ አለው” የሚል ውንጀላም ሲቀርብበት ቆይቷል።
ከሕወሃት አመራሮች ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለውና በዶክተር ደብረጺዮን ቦርድ አመራርነት ሲተዳደር የነበረው ኢ ኤን ኤን መቀመጫውን አዲስ አበባ አድርጎ ወቅታዊ ጉዳዮችንና የመዝናኛ ይዘት ያላቸውን ፕሮግራሞች ሲያቀርብ ነበር።

No comments:

Post a Comment