Monday, June 25, 2018

ኤፍ ቢ አይ በቦምብ ፍንዳታው ምርመራ ላይ እገዛ ያደርጋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 18/2010) በአዲስ አበባ ባለፈው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ የፈነዳውን ቦምብ በተመለከተ የአሜሪካው የምርመራ ተቋም /ኤፍ ቢ አይ/ በምርመራው እገዛ እንደሚያደርግ ተገለጸ።
የአሜሪካው የፌደራል የምርመራ ቢሮ ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሃገራቸው ያልተገለጸ የውጭ ሃገር የምርመራ ባለሙያዎች ሒደቱን ለማፋጠን ኢትዮጵያ መግባታቸውን መንግስት አስታውቋል።
የቅዳሜውን የቦምብ ጥቃት ተከትሎ የተቀነባበረ ጥቃት መፈጸሙን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ “ኢትዮጵያ ከጀመረችው የፍቅርና የይቅርታ መንገድ ሊገታት የሚችል ሃይል የለም”በማለት ርምጃው የለውጥ ጉዞውን እንደማይገታ አረጋግጠዋል።
ምርመራው እንደተጠናቀቀም ጉዳዩ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን አስታውቀዋል። በዚሁም መሰረት የምርመራውን ስራ የሚያካሂዱ የውጭ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ መግባታቸው ተዘግቧል።
የአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮም በምርመራው ሒደት እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

ከቦምብ ፍንዳታው ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ 9 የአዲስ አበባና የፌደራል ፖሊስ ሃላፊዎችና ባልደረቦች ታስረዋል።
በአጠቃላይ የታሳሪዎቹ ቁጥር 30 መድረሱም ተመልክቷል። በቅዳሜው የቦምብ ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈው ሁለት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ እነሱም ወጣት ዮሴፍ አያሌውና ወጣት ጉሳ ጋዲሳ የተባሉ መሆናቸውም ታውቋል።
ሕይወታቸውን ያጡት ዮሴፍ አያሌው ወላይታ ሶዶ የተወለደ ሲሆን ጉሳ ጋዲሳ ደግሞ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ የተወለደ መሆኑም ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሟች ቤተሰቦችን ስልክ ደውለው ማጽናናታቸውም ተዘግቧል።
ለሁለት ሰዎች ሞትና ወደ 160 ለሚሆኑ መቁሰል ምክንያት በሆነው የቦምብ አደጋ ሰለባ ለሆኑ ወገኖች የአዲስ አበባ መስተዳድር የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማም በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ ከታደመበት እጅግ ደማቅ ትዕይንተሕዝብ ባሻገርበጎንደር፣ ድሬደዋ፣ ደሴ፣ ጅጅጋ፣ ወልዲያ፣ ደብረማርቆስ፣ ወሮታ፣ ኮምቦልቻና አሳይታን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ የተደረጉ ትዕይንተ ሕዝቦች በሰላም ተጠናቀዋል።

No comments:

Post a Comment