Thursday, June 28, 2018

በኢትዮ-ሶማሊ ክልል ነዳጅ የማውጣት ስራ ቢጀመርም፣ የሶማሊ ክልል ተወላጆች ቅሬታ እንዳላቸው እየገለጹ ነው።

(ኢሳት ዜና ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ተወላጆች ለኢሳት እንደገለጹት የአገራችንን ሃብት መጠቀም መጀመሩ ጥሩ ቢሆንም፣ በአካባቢው ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ትኩረት አለማግኘቱን፣ በበቂ ሁኔታ የአካባቢ ጥበቃ አለመደረጉ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ህዝቡ ውይይት እንዲያደርግበት አለመጋበዙ ቅር አሰኝቶናል ብለዋል። ከድፍድፍ ማውጫ ግንባታው ጋር በሽላቦ አካባቢ ከፍተኛ የግጦሽ መሬት ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ፣1 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ በአካባቢው ጉዳይ ላይ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት አቶ ጀማል ድሬ ካሊፍ ገልጸዋል። ከነዳጁ በፊት በሶማሊ ክልል የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊቆም ይገባ ነበር ያሉት አቶ ጀማል፣ ኢትዮጵያውያን የዚህን ህዝብ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሰሙለት ይገባል ብለዋል። ጸሃፊና አክቲቪስት ሙስጠፋ ኡመር በበኩሉ ነዳጅ መውጣቱና አገሪቱ ተጠቃሚ መሆኗ ችግር ባይኖረውም፣ አሁንም አብዲ ኢሌ በስልጣን ላይ እያለና ህዝቡ ስለጉዳዩ በደምብ ሳያውቅ ነዳጅ እንዴት ሊወጣ ይችላል? የሚለው ነገር፣ ብዙዎችን እያነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል። ጠ/ሚኒስትር አብይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ብዙ ለውጦችን እያመጡ ባለበት ሁኔታ የሶማሌ ክልል በተበላሸ አስተዳደር ባለበት ሲረግጥ ለምን ዝም አሉት? የሚል ከፍተኛ ጥያቄ አለ ሲሉም አቶ ሙስጠፋ አክለዋል።

No comments:

Post a Comment