Monday, June 25, 2018

በሃዋሳ ከ200 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 18/2010) በሃዋሳ ከተማ በተነሳው ግጭት ለ10 ሰላማዊ ሰዎች ሞትና ለ80 ሰዎች መቁሰል ተጠያቂ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ከ200 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በግጭቱ 3ሺ 500 ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ሆስፒታል አልጋ ላይ የነበሩ ሰዎች ጭምር በጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውም ታውቋል።
የሲዳማ ዞን አስተዳደር አቶ አክሊሉ አዱላ አዲስ አበባ ለሚታተመው ሪፖርተር የእንግሊዝኛ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ በግጭቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ 226 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ግጭቱ የሲዳማንም ሆነ የወላይታን ሕዝብ የማይመለከት እንደሆነም አስተዳዳሪው ጨምረው ገልጸዋል።

ግጭቱ የብሔረሰብ አይደለም በሚል የተናገሩት የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዱላ የተፈናቀሉትን 4ሺ ያህል ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የሲዳማ ዞን አስተዳደር በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በተጓዙበት ወቅት በግጭቱ አካባቢ ያሉ የወረዳና የዞን ባለስልጣናት በፈቃዳቸው ስልጣን እንዲለቁ ያቀረቡትን ጥያቄ በተመለከተም ይህ በግል ውሳኔ የሚሆን አይደለም ሲሉ የሲዳማ ዞን አስተዳደሪ ምላሽ ሰጥተዋል።
በሕዝብ የተሰጠ ስልጣን በግል ውሳኔ መልቀቅ አይቻልም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትለው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪና ምክትል አስተዳዳሪን ጨምሮ የዞንና የወረዳ ባለስልጣናት በቅርቡ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment