Monday, June 25, 2018

በውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ላይ የተጠራው ዘመቻ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋረጠ

No automatic alt text available.(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 18/2010) በውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ላይ የተጠራውን ዘመቻ ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያውያን ግብረ ሃይል አስታወቀ።
ግብረሃይሉ ለኢሳት በላከው መግለጫ እንደገለጸው በአሁኑ ወቅት የህወሃት አገዛዝ ተጽዕኖ እየተዳከመና የፖለቲካ አመራሩ በለውጥ ፈላጊዎች እጅ የወደቀበት ሁኔታን ከግምት በማስገባት የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦው ዘመቻ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በለውጥ ቀልባሾች ሊደርስባቸው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ታሳቢ መደረጉን የገለጸው ዓለም አቀፍ ግብረሃይሉ ለስድስት ወራት የዘለቀው ዘመቻ በጊዜያዊነት መነሳቱ አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘው አስታውቋል።
አለም አቀፉ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረ ሀይል ላለፉት ስድስት ወራት የሬሚታንስ ተአቅቦ ዘመቻ ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

የዘመቻው አላማ የህወሃትን የኢኮኖሚ አቅም ማዳከም የነበረ መሆኑን የጠቀሰው የግብረ ሃይሉ መግለጫ በዚህ ረገድ ዘመቻው የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ብለን እናምናለን ብሏል።
ግብረሃይሉ አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ሁኔታ ዘመቻውን በተመለከተ ለውጥ እንዲኖር እንዳደረገ በመግለጽ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ዘመቻው መቋረጡን አስታውቋል። ከሶስት ወር ወዲህ የኢትዮጵያ ሁኔታ እየተቀየረ ነው።
በጎ የለውጥ ርምጃዎች እየታዩ ይገኛሉ። ለነዚህ በጎ ጅማሪዎች መከሰት ህዝባችን በደሙ እና በአጥንቱ የከፈለው መስዋእትነት ሲሆን የለውጥ ሂደቱን አሁን ካለበት ደረጃ በማድረስ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ቡድናቸው ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ሲል የዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል በመግለጫው ዕውቅና ሰጥቷል።
ምንም እንኳን የለውጥ ሂደቱ ህዝባችንን የስልጣን እና የሀገሩ ባለቤት ከማድረግ አኳያ በጣም ብዙ ደረጃዎች ቢቀሩትም፣ አሁን በታየው መጠነኛ ለውጥ እና ዶክተር አብይ ባስቀመጡት ራእይ ላይ በመመርኮዝ ህዝባችን ትልቅ ተስፋ ማድረጉን ተገንዝበናል ብሏል የግብረሃይሉ መግለጫ።
የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ዘመቻውን ጥሪ ተቀብሎ ሲታገል የነበረው የዲያስፖራ ማህበረሰብም የዚህ አገራዊ ተስፋ ተጋሪ ሆኗል ብሏል።
በመሆኑም የዲያስፖራውን የተስፋ ስሜት እና የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በማገናዘብ፣ የሬሚታንስ ተአቅቦው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ውሳኔ ላይ ደርሰናል ሲል ዓለም ዓቀፍ ግብረሃይሉ አስታውቋል።
ይህንን በማድረግ በአገራችን ውስጥ ላላው የለውጥ ጅማሮ ያለንን በጎ ስሜት እናንፀባርቃለን ብለን እናምናለን በማለትም ገልጿል።

No comments:

Post a Comment