Wednesday, June 27, 2018

በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ሰልፎች ቀጥለዋል ተባለ

Bildergebnis für dr.abiy ahmed(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 20/2010) በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በመደገፍ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ሰልፎች መቀጠላቸው ታወቀ።
ዛሬ በሆሳዕና በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ህወሃት ከደኢህዴን ላይ እጁን እንዲያነሳ ተጠይቋል።
ነገ በወልቂጤ ከተማ ተመሳሳይ ዓላማ ያለው የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ነዋሪው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በባህርዳርም ለፊታችን እሁድ የድጋፍ ሰልፍ የተጠራ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜናም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት እየታየ ያለውን የለውጥ ሂደት በመደገፍ ሰልፍ ሊያደርጉ መዘጋጀታቸው ታውቋል።
ዛሬ የሀዲያ ዋና ከተማ ሆሳዕና የድጋፍ ሰልፍ ማድረጓ ተሰምቷል። በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለመደገፍና ከቀልባሾች ለመታደግ በሚል የተጠራው የድጋፍ ሰልፍ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት የተወገዘበት መሆኑን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

ህወሀት ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ደኢህዴን ላይ እጁን እንዲያነሳ የጠየቀው የሆሳዕና ነዋሪ ደኢህዴንንም ራሱን ከህወሀት ጥገኝነት እንዲያላቅቅ ጥሪ ተደርጎለታል።
በሆሳዕና ስታዲየም በተደረገው በዚሁ በሰልፉ የተለያዩ መልዕክቶች ተስተጋብተዋል። ባንተባበር ተበልተን ነበር ፣ አብይ ሲመጣ ወኔያችን መጣ የሚሉና ሌሎች መፈክሮች በነዋሪው ዘንድ ሲነገሩ እንደነበረ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአልጀርሱ ስምምነት የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምላሽ እንደሚገኝለት በመግለጽ የሆሳዕና ነዋሪ መልዕክቱን አሰምቷል።
ከትላንት በስቲያ በደብረ ማርቆስ በተካሄደውና ተመሳሳይ ዓላማ ባነገበው የድጋፍ ሰልፍ ላይም በዋናነት ህወሀት መወገዙን ለማወቅ ተችሏል።
የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ ህወሀት እያደረገ ያለውን ሴራ እንዲያቆም የጠየቀው የደብረማርቆስ ነዋሪ በቅዳሜ የግድያ ሙከራ የተሰማውን ቁጣ ገልጿል።
በሚቀጥሉት ቀናት በወልቂጤና በባህርዳር የድጋፍ ሰልፎች እንደሚደረጉ ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።
በግጭትና አለመረጋጋት የሰነበተችው ወልቂጤ በነገው ዕለት ደማቅ ትዕይንት እያዘጋጀች መሆኗን ለማወቅ ተችሏል።
በወልቂጤው የድጋፍ ሰልፍ በኢትዮጵያ ህዝብ መሀል የእርስ በእርስ ግጭት የሚፈጥረውን ህወሀትን የሚያወግዙ መልዕክቶች ይሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጉራጌ ማህበረሰብ ከምንጊዜውም በላይ ህበረት አንድነቱን የሚያሳይበትና በኢትዮጵያዊነት ቀለም ደምቆ የሚታይበት የድጋፍ ሰልፍ እንደሚሆን አዘጋጆቹ ለኢሳት በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል።
በተያያዘ ዜናም የባህርዳር ነዋሪ ለፊታችህ እሁድ የጠራው የድጋፍ ሰልፍ ከከተማው አስተዳደር እውቅና ማግኘቱን ለማወቅ ተችሏል።
በባህርዳሩም የደጋፍ ትዕይንት እያበቃለት ያለው ህወሀት ከጥፋት ተግባሩ እንዲቆጠብ መልዕክት የሚተላለፍበት እንደሚሆን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
የባህርዳር ህዝብ በነቂስ በመውጣት ለለውጡ ድጋፉን እንዲያሳይና ለለውጥ አደናቃፊዎች ተቃውሞውን እንዲገልጽ አዘጋጆቹ ጥሪ አድርገዋል።

No comments:

Post a Comment