Monday, June 11, 2018

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ተመሰረተ

 (ኢሳት ዜና ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ/ም) በርካታ የክልሉ ተወላጆች በተገኙበት በባህርዳር ከተማ ሙሉአለም አዳራሽ በደመቀ ስነስርዓት የተመሰረተው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (ኢብን) የአማራን ህዝብ “ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ እና በተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ ህዝብ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን የመከላከል ዓላማ ይዞ “ መነሳቱን አሳውቋል። የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አማራው ሌሎች ወገኖችን በማስተባበር የአገሪቱን ነጻነት ማስከበሩን አውስተዋል። አማራው ከሌለው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተዋልዶ፣ ተዛምዶና ክፉ ደጉን አብሮ አሳልፏል ያሉት ዶ/ር ጫኔ፣ ባለፉት 50 አመታት ግን በጥራዝ ነጠቅ የተማሪዎች ንቅናቄ በባእድ ርዕዮተ አለም የአማራው ህዝብ የፖለቲካ ሸፍጥ እንተፈጸመበት ተናግረዋል። ባለፉት 50 አመታት በአማራ ህዝብ ላይ ለተፈጸመው ጥፋት ሁሉ ይህ የተሳሳተ የታሪክ ትርክት ምክንያት መሆኑን ሊቀመንበሩ አክለው ተናግረዋል። በአማራው ላይ ከፍተኛ በደል ሲደርስበት ቢቆይም አገራችን እንካሁን እንድትቀጥል ያደረጋት የአማራው ትዕግስት ነው ያሉት ዶ/ር ጫኔ፣ ትዕግስት ልክ አለው ፣ በአማራ ላይ የሚደርሰው በደል መቆም አለበት ብለዋል። አዲሱ ንቅናቄ ዶር ደሳለኝ ጫኔ-ሊቀመንበር፣ አቶ በለጠ ሞላ-ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ ጋሻው መርሻ-የድርጅት ጉዳይ፣ አቶ መልካሙ ሹምየ-የፖለቲካ ጉዳይ ሀላፊ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ 10 ሰዎችን በስራ አስፈጻሚነት መርጧል።

No comments:

Post a Comment