Friday, June 15, 2018

በወላይታ ሶዶ በተደረገው ተቃውሞ የሰዎች ህይወት ጠፋ

 (ኢሳት ዜና ሰኔ 8 ቀን 2010 ዓ/ም) በአዋሳ ከተማ የተካሄደውን የሲዳማ ማህበረሰብ አመታዊ የመን መለወጫ በአልን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት የተገደሉ ዜጎችን ድርጊት ለመቃወም ዛሬ በወላይታ ሶዶ በተካሄደው ተቃውሞ እስከ 5 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውን በርካታ የመንግስት መስሪያቤቶችና መኪኖች መውደማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። የሶዶ ከተማ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ የዞኑ ባለስልጣናት ፈቃድ በመከልከላቸው በቁጣ ገንፍሎ መውጣቱንና ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ማድረጉን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በኦሮሚያ ባንክ ዘበኛ የነበረ ሰው ወጣቶቹ በባንኩ አካባቢ ሲያልፉ ሁለት ወጣቶችን ተኩሶ መግደሉን፣ በዚህም የተነሳ የሕዝቡ ቁጣ አይሎ ወጣቶችን የገደለውን ዘበኛ ወጣቶች እንደገደሉት የአይን እማኞች ተናግረዋል። በርካታ ወጣቶችም ቆስለው ሆስታል ገብተዋል። በሃዋሳ የተነሳውን ግጭት ወደ ብሄር ግጭት ለመለወጥ የተደረገውን ሙከራ ተከትሎ ቁጥራቸውን በውል ያልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል። በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል። ወታደሮች ከተማዋን የተቆጣጠሩ ቢሆንም፣ አሁንም ውጥረት እንዳለ የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በከተማዋ ያለው የስልክ አገልገሎት በመቋረጡ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አልቻልም። መንግስት ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ሃይሎች በእየቦታው ግጭቶችን እያስነሱ መሆኑን ጠቅሷል። በእነዚህ ሃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ቢገልጽም፣ ለውጡን ይቀለብሳሉ የሚላቸውን ሃይሎች በዝርዝር አልገለጸም። አርበኞች ግንቦት7 ትናንት ባወጣው መግለቻ ደግሞ “የኢህአዴግ ፀረ-ለውጥ ኃይል የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ በሚያደርገው ጥረት የረዥም ጊዜ ተጎጂ ራሱ እንደሆነ መገንዘብ ይጠቅመዋል። ከእንግዲህ እንደቀድሞው ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ መግዛት አይቻልም፤ ከእግዲህ የሕዝብ ሀብት በግላጭ መዝረፍ አይቻልም። ይህን በጊዜ አለመገንዘብ ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፍላል። “ ብሎአል።

No comments:

Post a Comment