Tuesday, January 9, 2018

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ሃኪሞችን እና የሆስፒታል አመራሮችን ለማግኘት ለፍርድ ቤት ጽፈውት የነበረው ደብዳቤ ይፋ ሆነ

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ወርዶፋ ፣ ጥቅምት 22 ቀን 2010 ዓም ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት በጻፉት ደብዳቤ ሃኪሞችን እና የሆስፒታል አመራሮችን ለማግኘት ትእዛዝ እንዲጻፍላቸው ጠይቀው የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ግን ትዕዛዝ ሳይሰጥ ቀርቷል። 
ዶ/ር ፍቅሩ በደብዳቤያቸው “ ቀደም ሲል በሲውዲን ሃገር ሰርቼ ያገኘሁትን ገንዘብ እና 40 ዓመታት በልዩ የልብ ሕክምና ያዳበርኩትን እውቀት ይዤ ወደ ሃገሬ በመመለስ በሃገራችን ሁለት የልብ እና የልብ ነክ ሕክምና ሆሰፒታሎችን በማቋቋም ቀደም ሲል በህክምና እጦት ወደ ውጪ ሄደው መታከም ባለመቻላቸው ህይወታቸውን ያጡ የነበሩ የበርካታ ዜጎችን ህይወት መታደግ እንዲችሉ እና ባለፉት 11 ዓመታት ከ50 ሺ (ሃምሳ ሺ) ለሚበልጡ ዜጎች በአነስተኛ ዋጋ ህክምና እንዲያገኙ “ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

እነዚህን ሆስፒታሎች አሁንም ድረስ በቦርድ ሊቀመንበርነት እየመሩ እንደሚገኙ የገለጹት ዶ/ር ፍቅሩ፣ በርካታ ሃኪሞችን በራሳቸው ወጪ ሲውዲን ሃገር ልከው በማስተማር የዘርፉን እውቀት ወደ ኢትዮጵያ ሃኪሞች እንዲያሸጋግሩ አመርቂ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር ፍቅሩ “ ምትክ የሌለው ህክምና ለዜጎች በተሻለ አኳኋን እንዲሰጥ በአካል በቦታው ላይ ሆኜ መምራት ባለመቻሌ በቋሚነት ህክምና የሚደረግላቸው እና አዳዲስ ህሙማንን በሚመለከት በሆስፒታሉ ያሉ ሃኪሞች አገልግሎት እንዴት መስጠት እንዳለባቸው ለሃኪሞች የተሻለ ምክር መስጠት እንድችል ክቡር ፍ/ቤቱ የዜጎችን እጅግ ከፍተኛ ጥቅም ከግምት በማስገባት ቁጥራቸው እስከ አራት የሚሆኑ ባለሙያዎችን በቤተሰብ መጠየቂያ በኩል ቢመጡ የሚሰጠው የመነጋገሪያ ጊዜ እጅግ በጣም አጭር ደቂቃዎች ብቻ በመሆኑ ለማነጋገር አስቸጋሪ መሆኑን ከግምት በማስገባት ከእነዚህ ሃኪሞች እና የሆስፒታሉ አመራሮች ጋር በማረሚያ ቤቱ ቢሮ በኩል ተፈቅዶልኝ ከላይ ለተጠቀሰው በጣም አስፈላጊ ጉዳይ መገናኘት እንድችል እንዲፈቀድልኝ እና ለቂልንጦ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥልን በማክበር አመለክታለሁ፡፡” በማለት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ከደብዳቤው ለመረዳት ይቻላል።
የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ “ በእኔ መታሰር እና በከፍተኛ ጥበቃ ሆኜ እንዳክም ጠይቄ ስላልተፈቀደልኝ የሞቱት ታካሚዎቼ ቁጥር 20 ደርሰዋል።'' ሲሉ የመዳን ተስፋ የነበራቸው ታካሚዎች በስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች የጭካኔ ውሳኔ ምክንያት የእጅ አዙር ሞት እንደተፈረደባቸው ለችሎቱ መናገራቸው መዘገቡ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment