Wednesday, January 17, 2018

ታዋቂው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና ጨምሮ ከመቶ በላይ እስረኞች ተፈቱ

የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች የይቅርታ ስነስርዓቱ በሚፈቅደው መሰረት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ይፈታሉ በማለት ፣ የፌደራል ዋና አቃቢ ህግ ከተናገሩትየሚጣረስ መግለጫ ቢሰጡም፣ ዶ/ር መረራና የተወሰኑ እስረኞች ተፈተዋል። የገዢው ፓርቲ ልሳን የሆነው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል ዶ/ር መረራ በሁለት ቀናት ውስጥ ይፈታሉ ተብሎ የተዘገበው ስህተት ነው በማለት ነገሪ ሌንጮን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር። የኦፌኮ መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ በአውሮፓ ህብረት ተገኝተው የመንግስትን መልካም ስም አጥፍተዋል፣ ከአርበኞች ግንቦት7 መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተዋል እንዲሁም በኦሮምያ ባለው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እጃው አለበት የሚል ውንጀላ ሲቀርብባቸው ነበር።

ዶ/ር መረራ ከእስር ቢለቀቁም በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች አሁንም በእስር ቤት እየማቀቁ ነው። ታዋቂውን እና የተለያዩ ሽልማቶች አሸናፊ የሆነውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ፣ የኦፌኮ ም/ል ሊቀመንብር አቶ በቀለ ገርባ፣ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ አንዱአለም አራጌ እና ሌሎችም የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጥሪ አቅርበዋል።
ዶ/ር መረራ ከእስር ሲፈቱ በርካታ ወጣቶች ከፍተኛ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ዶክተር ሩፋኤል ዲሳሳም እንዲሁ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል።
በደቡብ ክልል ክሳቸዉ የተቋረጠ ተጠርጣሪዎች መካከል በመጀመሪያው ዙር 361 ሰዎች ተፈተዋል።
በጌዲዮ ዞን በሁከትና ብጥብጥ በመሳተፍ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 502 ተጠርጣሪዎች ውስጥ 361 ሰዎች የተለቀቁ ሲሆን፣ በ ኮንሶ ወረዳ በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር ከዋሉ 251 ተጠርጣሪዎች 52 ተጠርጣሪዎች በሚቀጥለው ሳምንት የተሀድሶ ስልጠና ወስደው እንደሚፈቱ የደቡብ ክልል አስታውቋል።
በሌላ በኩል የጀርመን ኢምባሲ የ ዶ/ር መረራ ጉድናን ጨምሮ በአዲስ አበባ ታስረው የነበሩ 115 እስረኞች መለቀቃቸው እንዳስደሰተው ገልጿል። “በኢትዮጵያ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ድምጻችው እንዲሰማና አሁን በአገሪቷ የሚታዩ ውጥረቶች ዘላቂ መፍትሔ ይገኝላቸው ዘንድ ቀጣይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኤምባሲው ያበረታታል።” ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።

No comments:

Post a Comment