Tuesday, January 23, 2018

ዓለም አቀፍ የክርስቲያን ኢትዮጵያውያን እህቶች ሕብረት በወልድያ በደረሰው እልቂት ሃዘኑን ገለጸ

 ህብረቱ ለኢሳት በላከው መግለጫ “ በመላው አለም የምንገኝ የወንጌላውያን አማኞች ቤተ/ክ ምእመናን እህቶች በወልድያ በደረሰው ዘግናኝ እልቂት የደረሰብን ሀዘን ከፍተኛ ነው።” ብለዋል፤፡
“ እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው፣ በየጊዜው እንደ ቅጠል ሲረግፍ ማየትና መስማት፣ የሁላችንንም ልብ የሰበረ ነው የሚለው ህብረቱ፣ በዚህ አሳዛኝ ጭፍጨፋ ምክንያት: ከማንም በላይ የሚጎዱት: ትውልድን አምጠው የወለዱ እናቶች፣ ጧሪ ያጡ ወላጆች፣ ወላጅ አልባ የሚሆኑ ሕፃናትና እነርሱ የሚደጉሟቸው ወገኖች በመሆናቸው: ይህ መከራቸው እኛን በሴትነታችን እጅግ እንዲሰማንና ሐዘናቸውን እንድንጋራ ግድ ብሎናል” ሲሉ ገልጸዋል።
እንደህ አይነት ዘግናኝ ግፍ የተሞላበትን ድርጊት የሚፈጽሙት ሁሉ ከዚህ ድርጊታቸው ይቆጠቡ ዘንድ የጠየቀው ህብረቱ፣ መንግስትም ይህን ድርጊት የፈጸሙትንም ሆነ ያስፈጸሙትን ለፍርድ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን ብለዋል። 
“በተለይም የወንጌላውያን አማኞች ቤተ/ክ ዝምታን መምረጣቸው ተገቢ ነው ብለን ስለማናምን፣ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉት ይህን አሳዛኝ ድርጊት እንዲኮንኑት እንጠይቃለን” በማለት ህብረቱ መግለጫውን ደምድሟል።

No comments:

Post a Comment