Tuesday, January 30, 2018

በወልድያ በርካታ የአገር ሽማግሌዎች ታሰሩ

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ገዱ አንዳርጋቸው ወልድያ ላይ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ሌሎችም ሰዎች እንደማይታሰሩ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ ከትናንት ምሸት ጀምሮ በርካታ የሃገር ሽማግሌዎች ቤታቸው እየተሰበረ ታስረዋል። አብዛኞቹ በሌሊት መታሰራቸውን ምንጮች ገልጸዋል። በአድማው ተሳትፈዋል የተባሉት ወጣቶችም እንዲሁ ታስረዋል። ነዋሪዎች ከትናንት ምሽት ጀምሮ 100 የሚሆኑ ወጣቶችና የሃገር ሽማግሌዎች በሌሊት እየታደኑ ተይዘዋል።
የአጋዚ ወታደሮች ከከተማው ለቀው እንደሚወጡ ፕሬዚዳንቱ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬም ተራራ ላይ ሰፍረው ጥብቅ ክትትል እያደረጉ ናቸው። አቶ ገዱ ቃል የገቡት ነገር አለመፈጸሙን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ይባስ ብሎ በእለቱ በስብሰባው ላይ አስተያየት የሰጡ ወጣቶች እንዲያዙ ምክንያት ሆነዋል በማለት ወቀሳ እያሰሙ ነው።

የከተማው ህዝብ ዛሬም የንግድ ድርጅቶችንና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመዝጋት ተቃውሞውን ሲገልጽ የዋለ ሲሆን፣ ተቃውሞው የታሰሩት እስኪለቀቁ እንደሚቀጥል ታውቋል። ከወልድያ ወደ ቆቦ የሚወስደው መንገድ አሁንም እንደተዘጋ ነው፡
በቆቦ ደግሞ ትናንት የአጋዚ ወታደሮች ወደ ወልድያ በኦራል መኪኖች ተጭነው ሲንቀሳቀሱ ወጣቶች መንገዱን ድንጋይ በመዝጋት እንዳይንቀሳቀሱ አድርገዋቸው ውለዋል።
በዛሬው እለት የከተማው ተወላጅ የሆነው አለምነው መኮንን በድጋሜ ህዝቡን በአዳራሽ ውስጥ ሰበሰበ ሲሆን፣ ህዝቡም አለምነውን አዋርዶ ስብሰባው እንዲበተን አድርጓል።
አቶ አለምነው የአካባቢው ተወላጅ ቢሆንም፣ አስተሳሰቡ ሁሉ የህወሃት መሆኑንና ተሰብሳቢዎቹ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል። ህዝቡ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳ ቢሆንም፣ አቶ አለምነው አጥጋቢ መልስ ባለመስጠታቸው ህዝቡ ስብሰባውን ትቶ ተበትኗል።
በቆቦም እንዲሁ አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ እንደተቋረጠ ነው። ነጋዴዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የህዝቡ ጥያቄ ካልተመለሰ ስራ አንጀምርም የሚል አቋም ይዘዋል።

No comments:

Post a Comment