Wednesday, January 3, 2018

የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ መባሉን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየቀረቡ ነው

ህወሃት/ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ዛሬ በጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት በሰጠው መግለጫ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲከኛ እስረኞች እንደሚፈቱ አስታውቋል። 
"በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችም የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወስነኗል::" ማለታቸውን የገዢው ፓርቲ ልሳናት ዘግበዋል።
በመግለጫው ላይ “አንዳንድ የፖለቲካ አባላትን ጨምሮ” የሚለው አገላለጽ ላይፈቱ የሚችሉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያመለክት መሆኑን አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
ክሳቸው የሚቋረጠው ወይም በይቅርታ የሚፈቱትም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንደሆነም መግለጫው አመልክቷል። 


ማዕከላዊ እስር ቤት ተዘግቶ ሙዚየም እንደሚሆንም መግለጫው አመልክቷል።
የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ የሚለውን ዜና ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጎ የነበረው የፖለቲካ ለውጥ አራማጁ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በሰጠው አስተያየት፣ ኢህአዴግ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ማለቱ የህዝቡ የትግል ውጤት መሆኑን ያሳያል ብሎአል ።
ህዝቡ እየጠየቀ ያለው የአገዛዝ ለውጥ ነው የሚለው አቶ ስንታየሁ፣ ኢህአዴግ ይህን የማያደርግ ከሆነ ተገዶ የስልጣን ለውጡ እውን ይሆናል ብሎአል። ህዝቡ የእስረኞችን መፈታት ድል እያጣጣመ ትግሉን መጨመር እና ለስርዓት ለውጥ መታገል እንደሚገባ አቶ ስንታየሁ ተናግሯል።
የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሃላፊ የነበረውና በቅርቡ ከእስር የተለቀቀው አቶ ዳንኤል ሽበሺ በበኩሉ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት አለባቸው መባሉ መልካም ዜና መሆኑን ገልጾ፣ በአዲስ አበባና በክልል ያሉ እስረኞች በሙሉ የሚፈቱ ከሆነ ደስታቸውን እንደሚጨምረው ተናግረዋል ።
የእስረኞች መፈታት የህዝቡን የፖለቲካ ጥያቄ የመልሰዋል ወይ ተብለው ለተጠየቁት ደግሞ፣ አቶ ዳንኤል “ ውሳኔው ጊዚያዊ ማስተፈንሻ እንጅ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አለመሆኑንና ትግሉ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በፌስቡክ ገጿ ላይ ባሰፈረችው ጽሁፍ ደግሞ “ ሲገድሉ፣ ጥፍር ሲነቅሉና ሲሸኑብን ከርመው ዛሬ ይቅርታ አድራጊዎች ሆነው ቁጭ አሉ። በዳይ ነው ወይስ ተበዳይ የይቅርታ ልብ ያለው? ... ይች እስረኞችን የመፍታትና ማዕከላዊውን ሙዚየም የማድረግ ዜና ለሥርዓቱ ትንፋሽ መግዥያ ከመሆን አታልፍም። ጎበዝ አትዘናጉ። እነእስክንድር ቢፈቱ የታሰረለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተፈትቷል ወይ? ለ6 ዓመታት መስዋዕትነት የከፈለው ለምን ነበር? ቤታችን የፈረሰው ለምን ነበር?” ብላለች።
ኢሳት ያነጋገራቸው ሌሎች ዜጎች ደግሞ ወያኔ ከመንበሩ ካልወረደ በስተቀር መሰረታዊ ለውጥ አይመጣም ይላሉ። ኢትዮጵያዊ ሁሉ በራሱ የጎበዝ አለቃ እየተመራ ትግሉን እያጧጧፈ የሚገኝ በመሆኑ፣ የመጨረሻው መደራሻ የስርዓት ለውጥ ብቻ ነው ይላሉ።

No comments:

Post a Comment