Tuesday, January 9, 2018

በኦሮምያ ወጣቶች እየታሰሩ ነው

ወጣቶቹ “የስርዓት ለውጥ እንፈልጋለን፣ አቶ ለማ ለውጡን ማምጣት ከቻለ ጥሩ ካልቻለ ግን እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” ይላሉ
በክልሉ ከሚካሄደው ያልተቋረጠ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ፣ የተለያዩ ወጣቶች እየተያዙ መሆኑን ኢሳት ያነጋገራቸው ወጣቶች ገልጸዋል። በኦሮምኛ ቄሮ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ለለውጥ በመታገል ላይ የሚገኙት ወጣቶች፣ የለማ መገርሳ አስተዳደር የክልሉን ወጣቶችን ከእስር እንዲታደግ ጠይቀዋል።
ወጣቶቹ እንደገለጹት በጉድሩ ወረዳ ባለፉት 6 ቀናት ከ 16 በላይ ተማሪዎች ተይዘው ታስረዋል። የታሰሩት ወጣቶች ቁጥር በርካታ መሆኑን የሚገልጹት ወጣቶች፣ የለማ አስተዳደር በአንድ በኩል የታሰሩትን እየፈታ በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶች እየታሰሩ መሆኑ ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል። 

በአካባቢው የሚታዬው ተቃውሞ አለመብረዱን የሚገልጹት ወጣቶች፣ መሰረታዊ ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ ተቃውሞው ይቀጥላል ብለዋል። የስልክ ግንኙነት መስመሮችን በመዝጋት ተቃውሞውን ለማዳፈን ሙከራ በማድረግ ላይ ያለውን የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝም ያረጀና ከእንግዲህ አገር ሊመራ የማይችል በመሆኑ ሊለወጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሰሞኑን የሰጡት መግለጫ ከአቶ ለማ አስተያየት በስተቀር አዲስ ነገር የለውም የሚሉት ወጣቶች፣ አቶ ለማም ቃላቸውን ወደ ተግባር አውልው ለህዝቡ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። በወሬ የተነገረውን መሬት ላይ ካላየነው፣ ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሚናገሩት ወጣቶች፣ ቄሮን ለማሰር እና ትግሉን ለማኮላሸት የሚደረገው ጥረት አይሳካም ይላሉ። ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ለውጥ መሆኑን የሚናገሩት የቄሮ አባላት፣ ስርዓቱ ያረጀ ስርዓት በመሆኑ በአዲስ መቀየር አለበት ይላሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝባዊ ተቀባይነታቸው እየጨመረ የመጣው አቶ ለማ መገርሳ ቃላቸውን በተግባር በመለወጡ ጉዳይ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ምንም እንኳ ለገና በአል በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ከእስር ቢፈቱም፣ ተቃውሞውን ያስተባብራሉ የተባሉ ወጣቶች መታሰር መጀመራቸው ብዙዎችን ግራ እያጋባ ነው። አቶ ለማ ስለዲሞክራሲ፣ ፍትህና ስለሰብአዊ መብቶች አያያዝ የተናገሩት የብዙዎችን ድጋፍ ቢያስገኝላቸውም፣ ንግግራቸው በአየር ላይ እንዳይቀር በክልሉ የተጀመረው የእስር ዘመቻ እንዲቆም፣ መከላከያው ከክልሉ ወጥቶ ህዝቡ በሰላም ተቃውሞውን እንዲገለጽ እንዲፈቀድለት ወጣቶች ጥሪ ያቀርባሉ።

No comments:

Post a Comment