Monday, October 2, 2017

የኢሬቻ በአል የህዝብ የተቃውሞ ማእከል ሆኖ ተጠናቀቀ

(መስከረም 22 ቀን 2010 ዓም) የኢሬቻ በአል የህዝብ የተቃውሞ ማእከል ሆኖ ተጠናቀቀ
በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የኢሬቻ በአል ህዝቡ በአገዛዙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ያሰማበት፣ አገዛዙ ላለፈው አንድ አመት ከላይ እስከታች ባካሄድኩት ጥልቅ ተሃድሶ ከህዝብ ጋር ስምምነት ላይ ደርሻለሁ በማለት ሲያሰራጨው የቆየው ፕሮፓጋንዳ ትክክል አለመሆኑን ያሳዬበት ሆኖ ተጠናቋል። በአሉን የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የሌሎች ብሄር ተወላጆችም በበአሉ ላይ በመገኘት ለኦሮሞ ወገናቸው ድጋፍ ከማሳየት አልፈው በተቃውሞው ተሳትፈዋል።

በኦሮምኛና በአማርኛ ቋንቋዎች “ወያኔ ይወገድ፣ ለውጥ እንፈልጋለን፣ ከሶማሊ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ፍትህ ይሰጣቸው፣ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ፣ አባይ ጸሃዬ ለፍርድ ይቅረብ ፣ በቀለ ገርባ ይፈታ፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና መሪያችን ነው ፣ ኦህዴድ አይወክለንም ፣ በሱማሌያ ክልል የሚፈናቀሉ ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰው የኦሮሞ ህዝብ ግፍ ይቁም ፣ መገደል ይብቃን” ” የሚሉና ሌሎች ስርዓቱን የሚያወገዙ በርካታ መፈክሮች በስፋት ተንጸባርቀዋል። አምና በነበረው ክብረ በአል ላይ “ወያኔ ይወደም” በእንግሊዝኛ “ ዳውን ዳውን ወያኔ” የሚለው መፈክር በመስከረም 21 ቀን 2010 ዓም በዚያው መድረክ ላይ የተደገመ ሲሆን የአገዛዙ ወታደሮች እና የደህንነት ሃይሎች እርምጃ ሳይወስዱ ውግዘቱን ለመስማት ተገደዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ ላይም እንዲሁ ተቃውሞው የተደረገ ሲሆን በአሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ ህዝቡ ተቃውሞውን እያሰማ ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ሌሎች ከተሞች በጭፈራ ተመልሷል።
በአሉን ለመታዘብ ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ የተጓዘ አንድ ወጣት፣ ባዬው ነገር ሁሉ በበአሉ ላይ ባዬው ነገር ሁሉ ስሜቱ መነካቱን ገልጿል። በአሉ በአጠቃላይ የተቃውሞ መገለጫ ሆኖ አልፏል ብሎአል።

እርሱ በተሳፈረበት መኪና ውስጥ “ አማራ መሆኑንና ኦሮምኛ መናገር እንደማይችል በተናገረበት ወቅት ወጣቶቹ ደስታቸውን እንደገለጹለት ተናገሯል።
በበአሉ ላይ አንድም የመንግስት ባለስልጣን ንግግር አላደረገም።

No comments:

Post a Comment