Tuesday, October 31, 2017

ወ/ት ንግስት ይርጋ በስር ቤት ኃላፊዎች ማስጠንቀቂያ እየተሰጣት መሆኑን ለፍርድ ቤት ተናገረች

በንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ በዓቃቤ ሕግ የሽብር ክስ የቀረበባቸውን ክስ አስመልክቶ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ ''ይከላከሉ ወይም በነጻ ይሰናበቱ'' በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለ3ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ፍርድ ቤቱ ብያኔው አልደረሰም በማለት ለህዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ወጣት ንግስት ይርጋ በስም ካስመዘገበቻቸው የቤተሰብ አባላት ውጭ እንዳትጠየቅ፣ እንዲሁም ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ባለው አንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ እንድትጠየቅ ገደብ የተጣለባት መሆኑን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታ ማቅረቧ ይታወሳል። ሀምሌ 21 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በቤተሰብ፣ የሃይማኖት አባት፣ የትዳር ጓደኛ እና በጠበቃዋ የመጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብት እንዳላት፣ የሰዓት ገደብም እና ልዩ ክልከላ ሊደረግባት እንደማይገባ ፍርድ ቤቱ ወስኖ ለቃሊቲ እስር ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም የቃሊቲ እስር ቤት ግን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለማክበር እስካሁን ፈቃደኝነቱን አላሳየም።

ፍርድ ቤቱ ነሃሴ 12 ቀን 2009 ዓ.ም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳላከበረ ኃላፊዎቹ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ ለዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ዛሬም ፍርድ ቤት አልቀረቡም።
ንግስት ይርጋ ፍርድ ቤቱ የላከው ትዕዛዝ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት መድረሱን ገልፃ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች እየጠሩ ''ለምን ማረሚያ ቤቱን ትከሻለሽ?' ከማን በልጠሽ ነው?'' እያሉ በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዳስጠነቀቋት ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች።
ፍርድ ቤቱም የንግስት ይርጋን አቤቱታ ከሰማ በኋላ "የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ፈፅመዋል ወይስ አልፈፀሙም የሚለውን ካጣራን በኋላ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፣ አልሰጡም የሚለውን የምናጣራ ይሆናል።" በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል ብላ ያቀረበችውን አቤቱታ ውድቅ አድርጎታል።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ወጣት ንግስት ይርጋን ስም በማዛባት ''ንግስቲ ይርጋ'' በማለት መጥራቱን እንዲያቆም እና ''ንግስት ይርጋ '' በማለት ማስተካከያ እንዲያደርግ ሲሉ የንግስት ይርጋ ጠበቃ ጠይቀዋል።
6ኛ ተከሳሽ አቶ ያሬድ ግርማ የማዕከላዊ እስር ቤት የምርምር ስራዎቹን ወስዶ እንዳልመለሰለትና ያቀረበው አቤቱታም መልስ እንዳላገኘ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል። ፍርድ ቤቱም በሌላ የክስ መዝገብ ምስክር ሊያሰማ መሆኑን በመግለፅ የሌሎች ተከሳሾችን አቤቱታ ሳይቀበል ቀርቷል።
5ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ በላይነህ ዓለምነህ በበኩላቸው "ለዚህ ቀነ ቀጠሮ የተሰጠን የራሳችን ሰዓት ተመድቦልን ስለሆነ በሌላ መዝገብ ምስክርነት አለ ልንባል አይገባም።" ሲሉ ቢያሳስቡም ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ሊቀበላቸው ፈቃደኛ አልሆነም። "ቢያንስ ችሎቱ ያለንን ሀሳብ እንድናስረዳ ዕድል ይፍጠርልን" በማለት በድጋሜ አቤቱታቸውን ቢያሰሙም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው በሌላ መዝገብ ወደያዘው ምስክርነት ገብቷል።
በእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ የተከሰሱት ንግስት ይርጋ፣ አለምነህ ዋሴ፣ቴዎድሮስ አታላይ ፣ አወቀ አባተ፣ በላይነህ ዓለምነህ እና ያሬድ ግርማ ናቸው።

No comments:

Post a Comment