Friday, October 27, 2017

በአምቦና አካባቢው በቀጠለው የለውጥ እንቅስቃሴ የአጋዚ ወታደሮች ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ

ረቡዕ ፣ ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓም የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬ ደም አፋሳሽ ሆነ ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ አምቦን አቋርጠው ወደ ክልሎች የሚሄዱም ሆነ በአምቦ መስመር ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ህዝቡ በወሰደው ሰላማዊ እርምጃ ተገተው ውለዋል።
ከፊንጫ ስኳር ጭነው ይወጡ የነበሩ መኪኖችን በማገት የተጀመረውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የአጋዚ ወታደሮችና የፌደራል ፖሊሶች ወደ አምቦ በብዛት ገብተው ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያደርገው ህዝብ ላይ እርምጃ የወሰዱ ሲሆን፣ እስካሁን ከ10 ያላነሱ ወጣቶች ሳይገደሉ እንዳልቀረ መረጃዎች ያመለክታሉ። የአጋዚ ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ የተበሳጩ ወጣቶች ድንጋይ በመወርወር ሁለት ወታደሮችን መግደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ትናንት ምሽት ድብደባ የተፈጸመባቸው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዛሬ ከህዝቡ ጋር በመቀላቀል ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። ( 01፡43-02፡55)
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ከአዲስ አበባ እስከ አምቦ በሚገኙ መስመሮች ላይ ቁጥጥር እያደረጉ ሲሆን፣ ተቃውሞው አድማሱን ሊያሰፋ ይችላል በሚል ፍርሃት በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ሳይቀር ፍትሻዎች እየተካሄዱ ነው።
በሌላ በኩል በኢሊባቦር መቱ ከተማ ኪሮስ ሆቴል ውስጥ የተለያዩ የጦር መሳርያዎች፣ የኦነግ አርማዎች እንዲሁም በራሪ ወረቀቶች ተገኝተዋል።
ከሩሃማ ሆቴል ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ሽጉጦች፣ ቦንቦች እንዲሁም ክላሽንኮቭ ጠምንጃዎች ተይዘዋል።
በምስራቅ ሃረርጌም ፈዲስ እና በደኖ ላይ እንዲሁ ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓም 7 ሰዎች በህዝብ ጥቆማ ተይዘዋል። ግለሰቦቹ ከድህንነት አባላት የተላኩና በአካባቢው በህዝብ መካከል ግጭት ለማቀጣጠል የተላኩ መሆናቸውን አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የኦህዴድ ባለስልጣን ለኢሳት ተናግረዋል። ከተያዙት ሰዎች መካከል በአንደኛው ሰው እጅ 25 ሺ ዶላር ተይዟል። ሌሎችም እንዲሁ ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጥ ያደረጉት ሰነዶች ተይዞባቸዋል። ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓም ባቢሌ ላይ የመንግስት ሰራተኞች በተሰበሰቡበት ቦንብ ይዞ በመግባቱ መያዙን ታውቋል።
በሌላ ዜና ደግሞ ከ 4 ወራት በላይ ያስቆጠረዉ በአማሮ ወረዳ የሚታየው ግጭት መቀጠሉ ታውቋል። በአካባቢው የአጋዚ ወታደሮች፣ የፌደራል ፖሊሶችና የደቡብ ክልል ፖሊሶች የሚገኙ ቢሆንም ግጭቱ አለመቆሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በዚህ ሳምንት ውስጥ ጉሙሬ በተባለዉ ቀበሌ የ15 አመት ወጣት፣ ዳኖ በተባለ ቀበሌ አንድ አርሶ አደር፣ ትናንት ደግሞ ሻሮ በተባለ ቀበሌ አንድ ሰዉ ሲገደል፣ ዶርባዴ በተባለ ቀበሌ ደግሞ አንድ አርሶ አደር እግሩን በጥይት ተመቶ የአጥንት ስብራት ደርሶበት ወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል እየታከመ ይገኛል። ከሻፉሌ ቀበሌ ከ20 በላይ ከብቶች እንደተዘረፉና ከጀሎና ዶርባዴ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ምንም እገዛ ሰላላገኙ በከፍተኝ ስቃይ ዉስጥ እንዳሉ፤ ከአማሮ ዲላ የሚወሰወደዉ መንገድ እስከ ዛሬ ዝግ በመሆኑ የወረዳዉ ህዝብ ለተጨማሪ ስቃይ እንደተጋለጠ፣ የ መብራትም አግልግሎትም ለወራት እንደተቋረጠ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ደቡብና ኦሮምያ ክልሎችን ድንበር እንለያለን በማለት የአካባቢው ባለስልጣናት ያስነሱት ግጭት በሺዎች ለመቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment