Monday, October 9, 2017

ባለፉት 3 ቀናት በኢትዮጵያ ሶማሊ እና በኦሮምያ ክልል ድንበር መካከል ያለው ግጭት እና ተቃውሞ ተባብሶ ሲቀጥል የመንግስት ባለስልጣናት ግራ ተጋብተዋል

(ኢሳት )ባለፉት 3 ቀናት በኢትዮጵያ ሶማሊ እና በኦሮምያ ክልል ድንበር መካከል ያለው ግጭት እና ተቃውሞ ተባብሶ ሲቀጥል የመንግስት ባለስልጣናት ግራ ተጋብተዋል
ባለፉት ሶስት ቀናት ምስራቅ ኦሮምያ በተለያዩ ተቃውሞዎች ሲናጥ ሰንብቷል። ተቃውሞዎች በአንድ በኩል የህወሃቶችን አጀንዳ እያስፈጸሙ ነው የሚባሉት የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ባለስልጣናትን በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸሙትን ግድያና ማፈናቀል እንዲያቆሙ የሚጠይቅ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተሻለ አስተዳደርና ፍትህ የሚያመጣ ስርዓት እንዲቋቋም የሚጠይቁ ናቸው።
በምስራቅ ሃረርጌ በጫት ምርታቸው የሚታወቁ ከተሞች እንቅስቃሴያቸው ተቋርጧል። “ጸሃይ አይጠልቅባትም” በምትባለዋ አወዳይ፣ ማንኛውም እንቅስቃሴ ቆሟል። በከተማዋ ከዚህ በፊት ይታይ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቆሟል። ወደ ሶማሊ ክልል የሚላከው ጫት በህዝቡ ውሳኔ እንዲቆም መደረጉን ነዋሪዎች ይናገራሉ። በሶማሊ ክልለ ከፍተኛ የጫት እጥረት መግባቱን ተከትሎ፣ ቀደም ብሎ ከኦሮምያ የሚመጣው ጫት መርዝ እንደተረጨበት አድርገው ሲሰብኩ የነበሩት የክልሉ ፕሬዚዳንት ፣ ከኦሮምያ የሚመጡ ጫት የጫኑ መኪኖች ጅጅጋ ሳይገቡ ቦምባስ ላይ እንዲያራግፉ የሚል ትእዛዝ በመስጠት በክልሉ የተፈጠረውን የጫት እጥረት ለመፍታት በማሰብ አቋማቸውን ቢያለዝቡም፣ የአካባቢው ወጣቶችን እንደተፈናቃይ ወገኖቻችን ሁሉ በችግር ተቆራምደን እንኖራለን እንጅ፣ ከእንግዲህ ጫት ወደ ሶማሊ ክልል አይላክም የሚል ጠንካራ አቋም በመያዛቸው ችግሩን ቀጥሎአል። በጨለንቆ ወረዳ ጫት የጫኑ ሁለት መኪኖች በወጣቶች ተሰባብረዋል።
ትናንት እሁድ መስከረም 27 ቀን 2010 ዓም በኩርፉ ጨሌ ወረዳ በነበረው ተቃውሞ ሽሪፍ አህመድ እና አብዱረዛቅ አህመድ የሚባሉ ወንድማማቾች በጥይት ተመትተው ሃረር ከተማ ውስጥ ህይወት ፋና ሆስፒታል ገብተዋል። ወጣት ሸሪፍ ጥይት በአፍንጫው ገብቶ በጉሮሮው ላይ የወጣ ሲሆን፣ ወንድሙ አብዱራዚቅ ደግሞ ታፋው አካባቢ ተመትቷል።
እንዲሁም መሃመድ በከር፣ አብዱላዚዝ አብዱላሂድና ኢብራሂም ጉቱ የተባሉት ወጣቶች ከኮምቦልቻ ወረዳ በጥይት ተመትተው በዚሁ በህይወት ፋና ሆስፒታል ተኝተዋል። አህመድ ኑር አብዲ በያንም እንዲሁ ጭንቅላቱ አካባቢ ተመትቶ ተኝቷል። የ70 አመቷ እናት ወ/ሮ ሃዋ መሌ እና አህመድ ሲራጅ ደግሞ ከባቢሌ ወረዳ ተመትተው ሆስፒታል ገብተዋል። አማን መሃመድ እና ፈርሃን እንድሪስ የተባሉት ወጣቶችም እንዲሁ በሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት ተመትተው ሆስፒታል ገብተዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሆስፒታሉ ሰራተኞች እንዳሉት በየቀኑ በጥይት እየተመቱ የሚመጡ ወጣቶች ቁጥር አልቀነሰም። በሆስፒታሉ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች፣ ሁኔታው ከሚሸከሙት በላይ እየሆነባቸው ተስፋ በመቁረጥ ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በምስራቅ ሃረርጌ የሚታየው የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ በሃረሪብሄራዊ ሊግ ላይም ያነጣጠረ ነው። ባለፈው ቅዳሜ ፣ መስከረም 26 ቀን 2010 ዓም በድሬ ጥያራ ወረዳ ፣ ግችት ቀበሌ በነበረው ተቃውሞ አንድ ወጣት በሃረሪ ፖሊሶች በጥይት ተመትቷል። በፈዲስ ወረዳም እንዲሁ አንድ ወጣት በቀበሌው ሊቀመንበር ተገድሏል። ህዝቡ የገዳዩን ሱቅ በማቃጠል የአጸፋ እርምጃ ወስዷል።
በሶማሊ ክልል እና በኦሮምያ ክልል መካከል ያለው ግጭት እንዲቆም ተደጋጋሚ ጥያቄና ማስጠንቀቂያ ቢያቀርብም፣ ግጭቱ አለመቆሙን በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ይመራል የሚባለው የፌደራል መንግስቱ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት አስታውቋል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሁለቱን ክልል ባለስልጣናት ጠርተው ቢያነጋግሩም፣ ከሶማሊ ክልል በኩል ፕሬዚዳንቱ አቶ አብዲ ሙሃመድ ሲገኙ፣ በኦሮምያ ክልል በኩል ፕሬዚዳንቱ አቶ ለማ መገርሳ ሳይገኙ ምክትላቸው ዶ/ር አብይ አህመድ ተገኝተዋል። አቶ ለማ መገርሳ ለምን በውይይቱ ላይ እንዳልተገኙ የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ አቶ ለማ ጠ/ሚኒስትሩ በጠሩት ሰብሰባ ላይ ምክትላቸውን በመላክ ለመገኘት አለመፈለጋቸው፣ ጠ/ሚኒስትሩ አቅም እንደሌላቸው ለማሳየት ወይም ንቀታቸውን ለመግለጽ ያደረጉት ሊሆን ይችላል።
አቶ ሃይለማርያም ከ100 ሺ ያላነሰ ህዝብ የተፈናቀለበት ግጭት እንዲቆም ከመማጸን ውጭ የተፈናቀሉት ዜጎች ወደ ተፈናቀሉበት ቦታ እንዲመለሱ እንዲሁም ወንጀሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ያነሱት ሃሳብ የለም።
አቶ ሃይለማርያምም ሆነ የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት የሶማሊ ክልል በቅርቡ ያወጣው መግለጫ ተገቢ አይደለም በማለት ክልሉ እንዲህ አይነት መግለጫ ከማውጣት እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።
የፖለቲካ ግለቱ እየጨመረ በህወሃት ዙሪያ የሚሽከረክሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እርስ በርስ እየተካሰሱ በመጡበት በዚህ ወቅት፣ አፈ ጉባኤ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አባ ዱላ ገመዳ የስልጣን መልቀቂያ አቅርበዋል። ስልጣን የለቀቁበትን ምክንያት ለወደፊቱ እንደሚገልጹ ቢናገሩም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የአገሪቱ የፖለቲካ ችግር ዋና ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
አባ ዱላ “ አሁን በደረስኩበት ደረጃ በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ሁኔታዎች ስሌለሉና ፍላጎቱም ስለሌለኝ ለመልቀቅ ድርጅቴንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጠይቄያለሁ፡፡” የሚል መግለጫ ሰጥተዋል።
በኢህአዴግ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ ሽኩቻ እንዲሁም ለሁለት አመት የዘለቀው ተቃውሞ መዳረሻው የት ይሆን በሚል በርካታ ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎችን እያነሱ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች በአገር ውስጥ ያለው ሁኔታ አስፈሪ መሆኑን ሲናገሩ ሌሎች ወገኖች ደግሞ በስርዓት ከተያዘ መልካም አገጣሚዎችን ይዞ መምጣቱን ይገልጻሉ። ተቃውሞዎች እየተጠናከሩ በሄዱ መጠን ስራዎች እየቆሙ የአገሪቱም ኢኮኖሚ ክፉኛ እየደቀቀ በመሄድ ላይ በመሆኑ፣ ይህም ሌላ ማህበራዊ ችግር ይዞ ሊፈጥር እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ። በምስራቅ ሃረርጌ ጫት ወደ ኢትዮጵያ ሶማሊና ወደ ጎረቤት አገሮች እንዳይላክ መደረጉ፣ የኢኮኖሚውን ችግር ያባብሰዋል የሚል ስጋት በአገዛዙ በኩል ተፈጥሯል። ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው የጫት ገበያ ንግድ መስተጓጎሉ አገዛዙን ስጋት ላይ ጥሎታል።
(ኢሳት ዜና መስከረም 28 ቀን 2010 ዓም)

No comments:

Post a Comment