Tuesday, October 3, 2017

የጎንደር ከተማ ነጋዴዎች የግብር ጥያቄያቸው ለዓመታት ባለመፈታቱ በርካታ ላኪ ነጋዴዎች ስራ ማቆማቸው ተነገረ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 23/2010)የጎንደር ከተማ ነጋዴዎች የግብር ጥያቄያቸው ለዓመታት ባለመፈታቱ በርካታ ላኪ ነጋዴዎች ስራ ማቆማቸው ተነገረ
ሰሞኑን በጎንደር ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት የከተማው ንግድ ዘርፍ ማህበራት ተጠሪ እንዳስታወቁት በርካታ ላኪ (ኤክስፖርተር) ባለሃብቶች ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ስራ ማቆማቸውን ገልጸዋል፡፡ይህ የሆነው በተደጋጋሚ የጠየቁት የግብር አወሳሰን ችግር እንዲስተካከል ጠይቀው ምላሽ በማጣታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ የጥራጥሬና እህል ላኪዎች፣ የቡና ንግድ ጅምላ ነገዴዎችና ላኪዎች ከ2003 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ጥያቄያቸው እየተገፋ በመሄዱ ስራ ለማቆም መገደዳቸውንና በየዓመቱ ንግድ ፈቃዳቸውን ብቻ በማሳደስ ፍትህ እየጠየቁ መሆኑን የዘርፍ ማህበሩ አመራራር ተናግረዋል፡፡
የንግድ ዘርፍ ማህበሩ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት አካላት ቢያስታውቁም ችግሩ ሳይፈታ መዘግየቱን የሚገልጹት የነጋዴዎች ተወካይ፣ የገዥው መንግስት አመራሮች ጥናታዊ ጽሁፍ አጥንተው እንዲያቀርቡ ጠይቀው ይህንኑን ቢፈጽሙም፣ ችግሩ ሳይፈታ ለሰባት ዓመታት መዘግየቱ ከተማዋ ብሎም ክልሉና ሃገሪቱ ልታገኝ የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ አንዳስቀረ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ከዘጠና አምስት በላይ የሆኑት የቡና ንግድ ላኪ ነጋዴዎች በደረሰባቸው የግብር ተጽዕኖ ስራቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ ከነዚህም መካከል መስራት ባለመቻላቸው አስራ ሁለት ነጋዴዎች ከኢትዮጵያ ውጭ መሰደዳቸውን፣ በሀገር ውስጥ ሰርቶ ለመኖር ያለው ምህዳር የተፈቀደው ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ እየሆነ መሄዱን እንደሚያመላክት የገለጹት የነጋዴዎች ተወካይ፣ ሆን ተብሎ በጎንደር ከተማ ነጋዴዎች ላይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ችግሮች ይፈታ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢው የንግድ ዘርፍ ማህበራት ተወካይ አክለው እንደገለጹት ከሆቴል ደረጃ ጋር በተያያዘ ከሁለት ዓመት በፊት እዲስተካከል የተጠየቀው ጥያቄ ሰሚ በማጣቱ የሆቴል ቤት ነጋዴዎችን ከስራ ውጭ እያደረገ ነው፡፡
“በጎንደር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች 75 በመቶ ሁልጊዜም አልጋ ያስይዛሉ” በሚል የወጣው የግብር መጠየቂያ ደንብ አብዛኛውን ሆቴሎች ስጋት ውስጥ የጣለ እንደሆነ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢ፣ መመሪያው ተስተካክሎ እንደ ሆቴሎቹ አሰራርና ዓይነት በየደረጃው የሚጠና ግብር እንዲጣል ቢጠይቁም ለዓመታት ምላሽ ማግኘት አልቻሉም፡፡
ይህ አሰራር የንግዱ ማህበረሰብ በስራው ላይ እንዳይቆይ ለማድረግ የተወጠነ ሰራ እንደሆነ የሚናገሩት ተወካይ፣ ከዚህ ባለፈም ገና ያልተሰራበትን የአመት ግብር በመመሪያው መሰረት በሚል በመጣል ነጋዴው እንዲሳቀቅ እየተደረገ መሆኑን አጋልጠዋል፡፡

No comments:

Post a Comment