Tuesday, October 24, 2017

(ኢሳት ዜና ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓም) በኢሉ አባቦር ዞን ጮራ ወረዳ ተፈናቅለው በአባጉሮ ከተማ የሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየጠየቁ ነው።

ተፈናቃዮቹ ለኢሳት እንደገለጹት ሰሞኑን በባለስልጣናት ቅንብር በተነሳው ብሄርን ማእከል ባደረገ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ሌሊቱን በሰላም አሳልፈዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች የደረሰባቸውን ጥቃት ተከትሎ አካባቢያቸውን በመልቀቅ አንጻራዊ ሰላም ወደ ስፈነባት አባ ጋሮ ከተማ በመሰደድ በከተማዋ ተጠልለው ይገኛሉ።
የአገር ሽማግሌዎች ከተፈናቃዮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ተፈናቃዮቹን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ እየሰሩ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።
ምንም እንኳ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ሽማግሌዎች እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴ መልካም ቢሆንም፣ እስከሚመለሱበት ቀን ድረስ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም ቤቶቻቸውና ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ሰዎች፣ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርግላቸው ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ግን ሌሊቱን 4 ቤቶች ተቃጥለው ማደራቸውንና ሁለት ሰዎች በጥይት መመታታቸውን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ግጭቱ ሙሉ በሙሉ አለመቆሙንም ገልጸዋል።
በክልሉ ውስጥ የሚካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ አንዳንድ ጥቅማቸው የተነካባቸው ሰዎች እንዳስነሱት የኦሮምያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እየገለጹ ቢሆንም፣ በስም ወይም በድርጅት ደረጃ ጠቅሰው መግለጫ ለመስጠት አልደፈሩም።
አንዳንድ ምንጮች ኢህአዴግን በመሰረቱት 4 ድርጅቶች መካከል ያለው የስልጣን ሽኩቻ እየበረታ መሄዱን በተለይም የህወሃት ደህንነቶች ከተወሰኑ የኦህዴድ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ግጭቶችን በየቦታው እየፈጠሩ እንደሆነ ይናገራሉ። አንዱ ሌላውን ቡድን መትቶ ለመጣል በሚደረግ ግብግብ፣ ህዝቡ ሃላፊነት የማይሰማቸው ባለስልጣናት በሚሸርቡት ሴራ ወጥመድ ውስጥ ባለመግባት የእርስ በርስ ግጭትን በማስቀረት ተቃውሞው በአገዛዙ ላይ ብቻ እንዲያነጣጥርም እየጠቁ ነው፡፡
በሌላ በኩል በአዳማ ከተማ ፣ገብረመድህን ይርጋው ገብረጊዮርጊስ የተባለ ግለሰብ 11 ሺህ 500 የአሜሪካን ዶላር ይዞ ሲንቀሳቀስ በፖሊስ ተይዟል። የክልሉ ፖሊስ እንዳስታወቀው ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ገንዘቡን ወደ ቶጎ-ውጫሌ ከተማ ለመጓጓዝ ሲዘጋጅ ነው።

No comments:

Post a Comment