Monday, October 23, 2017

ከኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ በኢሉባቦር አካባቢ የተከሰተውን አሳሳቢና አሳዛኝ ሁኔታ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

በአገራችን ውስጥ የተለያዩ ማህበረሰቦች ለዘመናት ተቻችለውና ተቀራርበው መኖራቸውንና እየኖሩም እንደሆነ ህዝቡ ራሱና ታሪክ ምስክር ናቸው። እነኚህ ማህበረሰቦች አብሮ ከመኖር ባሻገር የተጋቡና የተዋለዱ፤ ደስታና ሃዘናቸውን ሲጋሩ የኖሩም ናቸው። ይህ የአብሮነትና የመቻቻል መንፈስ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ እና   ወደፊትም የሚቀጥል ነው።


ይህንን የህዝባችንን የመቻቻልና አብሮ የመኖር የቆየ ሥርዓት ለራሱ የፖለቲካ ህልውና እንደ አደጋ የቆጠረው የህወሃት አገዛዝ፤ የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘም ሲል ወገንን ከወገን የማጋጨት ሴራ እየሸረበ መገዳደልንና ደም መፋሰስን እንደ ህልውና ማቆያ ስልት እየተጠቀመበት ይገኛል።
የህወሃት አገዛዝ ላለፉት 26 አመታት በህዝባችን ላይ የፈጠረውን አፈና ፤ ጭቆናና ብዝበዛ ለመቃወም ሰሞኑን በኢሉባቦር ዞን በቡኖ በደሌ ከተማና አካባቢው ተደርጎ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ አገዛዙ ሆን ብሎ ያሰማራቸው ሃይሎች የኦሮሞንና አብረውት የሚኖሩትን የሌሎች ብሄረሰብ አባላት በማጋጨት ግጭቱ ወደ እርስ በርስ  እንዲዞር እና የአስራ አንድ ንጽሃን ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ አድርጓል። በቅርቡ በሱማሌና በኦሮሞ ፡  በሲዳማና በኦሮሞ እንዲሁም በአፋርና በአማራ ህዝብ መካከል  ፈጥሮት የነበረውን ግጭት ማስታወስ ተገቢ ነው።
ህወሃት እንዲህ አይነት እኩይ ተግባር የሚፈጽመው ህዝባችንን በመከፋፈል ቆሞበት የነበረው የፖለቲካ መሠረት ስለተናጋበትና ቀደም ሲል የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲጠቀምባቸው የነበሩት የኢህአደግ አባል ድርጅቶች በተለይም ኦህዴድና ብአዴን ከተገፋው ህዝባቸው ጎን የመቆም ዝንባሌ ማሳየት በመጀመራቸው የሥልጣን ዕድሜው እያጠረ መሆኑን በመገንዘቡ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። ከዚህም በተጨማሪ እራሱ በሚቀሰቅሰው ግጭት የሚፈጠረውን የሰላምና መረጋጋት እጦት በመጠቀም የለመደውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም አገሪቱን ወደ ወታደራዊ አገዛዝ የመመለስ ዕቅዱን ለማሳካት ነው።
የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ህወሃት የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲል እየተጓዘበት ያለውን  ይህን እኩይ ተግባር አጥብቆ ያወግዛል። ግጭት በመቀስቀስ ለፈሰሰው የዜጎች ደም ህወሃት ብቸኛ ተጠያቂ እንደሆነም ያስገነዝባል።
እንዲህ አይነት ሃላፊነት  የጎደለው እርምጃ ተፋቅሮና ተቻችሎ የሚኖረውን ህዝብ ወደ እርስ በርስ ብጥብጥ በመውሰድ ወደ ማያባራ ጦርነት አገሪችንን ሊወስዳት እንደሚችል ህዝባችን አውቆ በህወሃት ሴራ ሳይጠለፍ ከአሁን ቀደም ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ እራሱን ፡ ቤተሰቡንና አካባቢውን ከእርስ በርስ ግጭት ተግቶ እንዲከላክል ንቅናቄያችን ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሚያ እና አማራ አካባቢዎች የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ በተቀረው የአገራችን ክፍሎች ሁሉ በማዳረስ አፈናና ጭቆና የሚያበቃበት ጊዜ እንዲመጣ መላው ህዝባችን የዚህ ህዝባዊ ትግል አካል እንዲሆን የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ተግቶ እንደሚሠራ ማስታወቅ ይወዳል።
በህወሃት የአፈና ተቋማት ውስጥ የምትሰሩ በተለይም የመከላክያ፡ የፖሊስና የደህንነት አባላት የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዚህ የመከራ ወቅት ከነጻነት ጠያቂው ወገናችሁ  ጎን እንድትሰለፉ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።
ፍትህ እና ነጻነት ለኢትዮጵያ ህዝብ !

No comments:

Post a Comment