Tuesday, October 31, 2017

በባህርዳር ከመደበኛ፣ ልዩ ሃይልና ከደህንነት ቢሮ የተውጣጡ የከፍተኛ መኮንኖች ህቡዕ ድርጅት ተመስርቷል የሚል ሪፖርት ቀረበ

ከክልሉ የደህንነት መስሪያ ቤት ባገኘነው መረጃ፣ ከአማራ ፖሊስ መደበኛ እና ልዩ ሀይል ከፍተኛ መኮነኖች እንዲሁም የክልል ደህንነት ቢሮ ሰራተኞች የተካተቱበት የህቡህ ድርጅት መመስረቱን የሚያመለክት ሪፓርት ቀርቧል ። የክልሉ የፖሊስ አባላት እና የደህንነት አባላት በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ደስተኛ ባለመሆን የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል። ትናንት የባህር ዳር የግንቦት 20 ክ/ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ የፖሊስ አባላት የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የዞን ፖሊስ የመረጃ ቡድን ሃላፊው ኮማንደር አትንኩት አያሌው “በእኔ ላይ የግድያ እርምጃ ሊወሰድብኝ” ነው በማለት ለክልሉ ምክትል ኮሚሽነር ደስየ ደጀኔ አቤቱታ በማቅረብ የአመት እረፍት እንዲሰጠው ቢጠይቅም፣ ምክትል ኮሚሽነሩ ግን “ በክልል ደረጃ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ እየተባለ ያለውን እና በተቋሙ ላይ ያለውን የህቡዕ አደረጃጀት የሚመረምር አካል እንኪዋቀር በስራህ ላይ ቀጥል” ብሎ አሰናብቶታል። ኮማንደር አትንኩት በአማራ ክልል በይበልጥ ደግሞ በባህርዳር ከተማ ወጣት ላይ ከፍተኛ ግፍ ፈፅሞአል በሚል በፖሊስ አባላቱ ቂም የተያዘበት ግለሰብ ሲሆን፣ የህቡዕ ቡድኑ የመጀመሪያ ኢላማ እኔ ነኝ የሚል ስጋት እንዳደረበትና ማስፈራሪያ እንደደረሰው ሪፖርት አቅርቧል። 

ከማንደር አትንኩት በቅርቡ ባህር ዳር ከተማ በፈነዱ ቦንቦች ምክንያት ምንም የማያውቁትን ወጣቶች ለብዙ ስቃይ የዳረገ ሰው ሲሆን፣ መቀመጫውን አዴት ከተማ ያደረገ የግንቦት 7 ሴል አባላት ናቸው በሚል ብዛት ያላቸው የባህርዳር ከተማ ወጣቶችን በመያዝ በተለያዩ የምርመራ ቦታዎች ከፍተኛ ስቃይ እንዲደርስባቸው አድርጓል።
የፖሊስ አባላቱን ህቡ አደረጃጀት ለመበተን በሚመሰል መልኩ ትናንት የግንቦት 20 ክ/ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ አባላት፣ ከላይ የመጣ መመሪያ ነው በሚል ሁሉንም አባላት ሊበታትኖአቸው መታቀዱን ሲነገራቸው፣ ምሽት ላይ ሁሉም የፖሊስ አባላት በጣቢያው ግቢ ውስጥ “ ስራ አንሰራም” በማለት አድማ አድርገዋል። ኮማንደር ዋለልኝ አባላቱ “የፖሊስ ስነ-ስርዓት እንዲኖራቸው” ቢጠይቅም፣ የፖሊስ አባላቱ ግን “እኛ ቤተሰብ ያለን ልጅ የምናስተምር ሆነን እያለ፣ ምንም ሳታማክሩን ወደ ተለያየ ቦታ ልታዛውሩን ማሰባችሁ ለእኛ ክብር እንደሌላችሁ ያሳያል” በማለት ተቃውመውታል።
የአማራን ልዩ ሀይል በፌደራል ደረጃ ለማዋቀር የተጀመረውን እንቅስቃሴ የሚቃወሙት የልዩ ሀይል አባላት፣ ውሳኔው በግድ ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ የራሳቸውን አማራጭ እንደሚወስዱ እያስጠነቀቁ ነው። ከሁለት ቀናት በፊት ጎርደማ ገብርኤል በሚገኘው የክልሉ የልዩ ሀይል ካምፕ በነበረው ስብሰባ፣ አባላቱ ፌስቡክ እና ኢሳት በሚነዙት አሉባልታ እንዳይደናገሩ፣ እንደ ፖሊስ ከላይ የሚመጣን ትእዛዝ ማክበር እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል። የክልሉ የፖሊስ አመራሮች ከክልል ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ፣ በልዩ ሀይል አባላቱ ላይ የመንፈስ መረበሽ እንዳለና በግልፅ ባይወጣም የፖለቲካ ጥያቄ በውስጣቸው እንዳለ መረዳታቸውን፣ በርካታ አባላቱ ፌስ ቡክ ተጠቃሚ በመሆናቸው የአሉባልታ ተጠቂ መሆናቸውን የሚጠቁም ነገር እያየን ነው በማለት ይህ የፌስቡክ ነገር መላ ካልተዘየደለት ወይም መመሪያ ካልወጣለት የአባሎችን ስነ ልቦና መፈታተኑን ይቀጥላል ብለዋል።
የአማራ ክልል ልዩ ሀይል አባላት የሌሎች ክልል የልዩ ሃይል አባላት የቡድን መሳሪያ ማለትም መትረጊስን ጨምሮ እያንዳንዱ አባል የራሱ የሆነ ክላሽንኮቭ እና የእጅ ቦንብ የሚይዝ ሆኖ ሳለ ፣ የአማራ ልዩ ሀይል አባላት ግን ለስራ ሲወጡ እንኳን ለ3 ሰው አንድ ክላሽ እና ለቀሪዎቹ ሁለት ፖሊሶች የፕላስቲክ ቆመጥ ብቻ እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ። የሱማሌ፣ የኦሮምያና የትግራይ ልዩ ሀይል አባላት በነፍስ ወከፍ፣ ክላሽ እና ቦንብ ተሰጥቷቸው እያለ፣ እነሱ ግን እጃቸው ላይ ምንም እንዳይዙ የተደረገው በህወሃት ሴራ ነው ብለው ያምናሉ።

No comments:

Post a Comment