Friday, October 27, 2017

ኢሳት ዜና ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓም) የአቶ በረከት ስምዖን የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ፣ የአቶ አባዱላ ገመዳ ግን ገና በውይይት ላይ እንደሆነ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በርካታ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ባወሱበት በፓርላማ ንግግራቸው፦” አቶ በረከት በተደጋጋሚ የመልቀቂያ ጥያቄ በማቅረቡ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቷል። ከክቡር አባዱላ ጋር ግን ገና እየተወያዬን ነው። ውሳኔው ምን እንደሚሆን በቅርቡ እናያለን” ብለዋል።
የኦህዴዱ አባዱላ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ የወሰኑት “የህዝቤና የድርጅቴ ክብር ተነክቷል” በማለት እንደሆነ ራሳቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሀን መግለጻቸው ይታወሳል።
አቶ አባዱላ ይህን ምክንያት ሰጥተው ኃላፊነታቸውን ቢለቁም ነገሮች እየባሱ እንጂ እየተሻሻሉ አልመጡም።
በአምቦ ትናንትና እና ዛሬ በርካቶች የተገደሉ ሲሆን፤የብሮድካስቲን ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዘርአይ አስግዶም ክብርን በሚነካ መልኩ በሥልጣን የሚበልጧቸውን የኦህዴዱን አመራርና የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩን መግለጫ በማጣጣል ለአባዱላ ድርጅት ያላቸውን ንቀት በትናንትናው ዕለት አሳይተዋል።
በሌላ በኩል አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዛሬው ዕለት ባደረጉት ንግግር ፦” ወደየትኛውም ክልል ብትሄዱ ሕዝባችን ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለው ፍቅር ልዩ መሆኑን ታያላችሁ” በማለት መናገራቸው በርካቶችን አስቆጥቷል።
በተለይ በዛሬው ዕለት በአምቦ ሕዝብ ላይ በመከላከያና በአጋዚ ይፋ ጦርነት በተከፈተበትና በርካቶች ሙትና ቁስለኛ በሆኑበት ጊዜ አቶ ኃይለማርያም ሠራዊቱ ሰብ ዓዊነት የተሞላና ህዝባዊ ፍቅር የተላበሰ እንደሆነ በፓርላማው መናገራቸው በቁስል ላይ ሆምጣጤ እንደመጨመር ነው ሲሉ ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲገልጹ ውለዋል።

No comments:

Post a Comment