Tuesday, October 10, 2017

በአማሮ ወረዳ የተጀመረው ግጭት የንጹሃንን ህይወት እያስከፈለ ቀጥሎአል

በአማሮ ወረዳ የተጀመረው ግጭት የንጹሃንን ህይወት እያስከፈለ ቀጥሎአል
የኦሮምያና ደቡብ ድንበርን እናካልላለን በሚል ባለስልጣናት ያስነሱት ግጭት ባለመብረዱ የአካባቢው ህዝብ በከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቋል። የኮሬ እና የጉጂ፣ የቡርጂና የጉጂ ማህበረሰብ አባላትን እርስ በርስ ለማጋጨትና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተደረገው ሴራ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለውና የእለት ደራሽ እርዳታ ጠፍቶ ከፍተኛ ችግር ላይ በወደቁበት በዚህ ጊዜ፣ ዛሬ ደግሞ መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎች ከአማሮ ወደ ዲላ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መኪና ላይ ባደረሱት ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ፣ ሾፌሩን ጨምሮ ሌሎች ሶስት ተሳፋሪዎች ደግሞ በጽኑ ቆስለው ወደ አርባምንጭ ሆስፒታል ተወስደዋል።
ኢሳት ትናንት ባቀረበው ዜና የመከላከያና የፌደራል ፖሊሶች መንገዱ ሰላም ነው በማለት ተሽከራከሪዎች ጉዞ እንዲጀምሮ ሲያስገደዱ እንደነበር ጠቅሶ ነበር። ይህንን ተከትሎ ህዝቡ ከጥቃት የማትታደጉን ከሆነ ከአካባቢያችን ውጡ በማለት የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አባላትን እየጠየቀ ነው።
በሌላ በኩል በአማሮ ወረዳ ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት የሚመዘገብ በመጥፋቱ የመከላከያ ባለስልጣናት በግጭቱ ወደ ተፈናቀሉ ወጣቶች በመሄድ፣ ወደ መከላከያ ግቡና ሰልጥናችሁ ስትመለሱ አካባቢያችሁን ለመከላከል ትችላላችሁ በማለት ወደ ውትድርና ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመራቸው እንዳስገረማቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። (ኢሳት ዜና–መስከረም 30/2010)

No comments:

Post a Comment