Monday, June 6, 2016

ደቡብ ጎንደር ፋርጣ ወረዳ በመንግስት ታጣቂዎችና በአካባቢው ህዝብ መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ

ኢሳት (ግንቦት 29 ፥ 2008)
እሁድ በደቡብ ጎንደር ፋርጣ ወረዳ ጉና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመንግስት ታጣቂዎችና በአካባቢው ህዝብ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ሰኞ ድረስ እልባት አለማግኘቱንና ድርጊቱ በአካባቢው ውጥረት አንግሶ መገኘቱን ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።
ከግጦሽ መሬት ጋር በተገናኘ ተቀስቅሷል የተባለው ይኸው ግጭት መልኩን በመቀየር በነዋሪው ዘንድ ተቃውሞ ማስከተሉን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ልዩ ስሙ ዋንቃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቀያቸውን በመተው ወደ ጫካ መሰደዳቸውን በድርጊቱ የተሳተፉ አንድ እማኝ አስታውቀዋል።
መሽገው እንደሚገኙና ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ አንድ አዛውንት እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች በእጃቸው ያለን መሳሪያ በማንገብ በስፍራው መመሸጋቸውን ገልጸዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎችና አድማ በታኝ ቡድን በአካባቢው ሰፍኖ መገኘቱን የተናገሩት እማኞች እሁድ ለሶስት ሰዓት ያህል ጊዜ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ አንድ ነዋሪ መገደሉን አክለው አስታውቀዋል።
በጉና ዙሪያ ወደ 10ሺ አካባቢ የሚጠጋ ነዋሪ የሚኖር ሲሆን አብዛኛው ህዝብ በዚሁ ተቃውሞ መሳተፉን ተሸሽገው የሚገኙት ነዋሪዎች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል።
ቦታችን እንዳይነካብን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ሲሉ የተናገሩት እነዚሁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መሽገው የሚገኙበት ስፍራ ጥቃት የሚሰነዘርበት ከሆነ እርምጃን እንደሚወስዱ አክለው አስታውቀዋል።
በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ስር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ከአስተዳደራዊ ጥያቄ ጋር በተገናኘ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ መሰንበታቸው ይታወሳል።
በጎንደር ጉና ዙሪያ ዋንቃ የተደረገው ይኸው ግጭት ወደ ሌሎች አካባቢዎች መስፋፋቱም ተነግሯል። በአካባቢውና በአጎራባች ያሉ ቀበሌዎች ከመንግስት ሃይሎች ጋር ተፋጠው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

No comments:

Post a Comment