Monday, June 13, 2016

ኤርትራ በጾረና ግንባር ጥቃት እንደተሰነዘረባት አስታወቀች

ሰኔ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ በጾረና ግንባር የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ትናንት እሁድ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ስለ ጥቃቱ ዝርዝር መግለጫ እንደሚያወጣ ገልጿል። በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም። በሁለቱም ድንበሮች ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየታዬ ሲሆን፣ ጥቃቱ ወደ ሙሉ ጦርነት ይሸጋገር አይሸጋገር ገና  የታወቀ ነገር የለም። አርበኞች ግንቦት7 ባወጣው መግለጫ ጦርነቱ ህወሃት ከገባበት የውስጥ አጣብቂኝ ለመውጣት የጀመረው ነው ብሎአል።

“የህወሃት ዘረኝነት በፈጠረው ኢፍትሃዊነትና አፈና የተማረረው ህዝባችን በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ማለት ይቻላል በአገዛዙ ላይ ተቃውሞውን እያጠናከረ ባለበት በዚህን ሰዓት በሙስና የተጨማለቁ የህወሃት የጦር ጀነራሎችና በስቪል ማዕረግ አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩ ሃይሎች ለምን ይህንን ጦርነት መጫር እንደፈለጉ ግልጽ ነው” የሚለው ንቅናቄው  ፣  በኦሮሚያ የተነሳው ህዝባዊ ንቅናቄ፣ የወልቃይት ህዝብ ያነሳው የማንነት ጥያቄ፣  የአርበኞች ግንቦት7 ታጋዮች በአርባምንጭ አቅራቢያ የፈጸሙት ጥቃት፣  በቤኔሻንጉል፤ በጋምቤላ ፤ በአፋርና በሱማሌ ከመሬት ንጥቂያ ጋር በተያያዘ በህዝቡና በአገዛዙ መካከል የተፈጠረው ልዩነት ህወሃት ፊቱን ወደ ሰሜን በጦርነት ስም በማዞር ትኩረት ለማስቀየስ እየሞከረ ነው ሲል አክሏል።
በአዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ቀድሞውኑም የድጋፍ መሠረት እንደሌለው የገለጸው ንቅናቄው፣  ይኩራራበት የነበረው የትግራይ ምሽግነም ከእጁ ሙሉ በሙሉ እያፈተለከ መምጣቱን ጠቁሟል።  ንቅናቄው በማከልም “በባድሜ ጦርነት የተከፈለው ዋጋና ከባድሜ ጦርነት መልስ ጉልበቱን አጠናክሮ ለመውጣት የቻለው የህወሃት አገዛዝ እስከዛሬ በህዝባችን ላይ እየፈጸመው ያለው አፈናና ጭፍጨፋ ተዘንግቶ ፣ ለወያኔ ዳግም ዕድል የሚሰጠ ኢትዮጵያዊ አይኖርም። “ ያለው አርበኞች ግንቦት7፣ “ወያኔ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘምና የተዘፈቀበትን የሃብት ዘረፋ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያደርገውን የሞት ሽረት ትግል ህዝባችን በምንም አይነት ሁኔታ ማስተናገድ የለበትም “ ሲል ጥሪ ያስተላልፋል።

No comments:

Post a Comment