Thursday, June 16, 2016

ኤርትራ ከ200 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገድላ ከ300 በላይ ማቁሰሏን አስታወቀች

ሰኔ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የህወሃት መንግስት ሰኔ 5 ቀን 2008ዓም  በጾረና ግንባር ጥቃት መጀመሩንና  ሰኞ ሰኔ 6 ጠዋት ላይ ለማጥቃት የተንቀሳቀሰው ጦር ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሁዋላ ማፈግፈጉን ገልጿል።

በዚህ አላማው ግልጽ ባልሆነ የግድየለሽ ጥቃት 200 የኢትዮጵያ ወታደሮች ሲገደሉ 300 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል ብሎአል። የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ ይቻላል ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።  ይህን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማካሄድ ለምን ተፈለገ? ምንስ ለማግኘት ነው ሲል የሚጠይቀው መግለጫው፣ ይህን ሃላፊነት የጎደለው ጥቃት እንዲጀመር ያነሳሱ ሃይሎች ከጥቃቱ በፊትና በሁዋላ ለህወሃት የፖለቲካ፣ የሚዲያና የዲፕሎማሲ  ሽፋን ለመስጠት ሞክረዋል ብሎአል። ጥቃቱን በጀመረውና ጥቃቱ በተፈጸመበት ላይ እኩል ወቀሳ መቅረቡንም መግለጫው አውግዟል። የኤርትራ መንግስት የጥቃቱን ስፋት በተመለከተ ተከታታይ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ኤርትራ የህወሃት መንግስት ጥቃቱን እንዲፈጽም ከጀርባ አነሳስተዋል፣ የሚዲያና የዲፕሎማሲ ሽፋን እንዲሰጠው አድርገዋል ያለችውን ሃይል ወይም ሃይሎች በስም አልጠቀሰችም። ይሁን እንጅ እስካሁን ድረስ  ሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳይገቡ ማስጠንቀቂያ ያወጣች ብቸኛዋ አገር አሜሪካ ናት።
ኤርትራ ያወጣችውን መግለጫ በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የተሰጠ መልስ የለም። የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በኤርትራ ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ ተወስዷል ሲሉ መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል። ወደ ዜና ከመግባታችን ትንሽ ቀድም ብሎ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባን ኪሙን  ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት እንዳይገቡ አሳስበዋል። የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆንም ዋና ጸሃፊው ጠይቀዋል።
ከ15 አመታት በፊት በሁለቱ አገራት መካከል ተደርጎ በነበረው ጦርነት ፣ በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው በጾረና በኩል ነበር። በወቅቱ ጦርነቱን እንደመሩት የሚነገርላቸው  አቶ ስዬ አብርሃ በጾረና ግንባር ለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ወቀሳ ድሮሳባቸው እንደነበር በጊዜው ይወጡ የነበሩ ጋዜጦች ዘግበዋል።
የህወሃት ደጋፊዎች የመከላከያ ሰራዊቱ በኤርትራ ላይ ሙሉ ጦርነት እንዲከፍት አሁንም ጥሪ እያቀረቡ ነው። ግጭቱ በተጀመረበት ሰኔ 5፣ በርካታ የህወሃት ደጋፊ ጋዜጠኞች “ ሙሉ ጦርነት ተጀመረ፣ አሰብን እናስመልስ” በማለት በማህበራዊ ሚዲያዎች ዘገባዎችን ቢያቀርቡም፣ በኢህአዴግ መንግስት በኩል ግን ተመጣጣኝ እርምጃ ወስደናል ከማለት ውጭ በጦርነቱ እንደሚገፋበት ፍንጭ አልሰጠም።
የኢህአዴግ መንግስት ከኤርትራ ጋር ለመታረቅ ተደጋጋሚ ሙከራ ማደርጉን ይገልጻል። ባድመን ለኤርትራ ለማስረከብ ፈቃደኛ መሆኑንም ይናገራል። የኢህዴግ መንግስት ባድመንም ሆነ ሌሎች በሄግ ፍርድ ቤት ለኤርትራ የተሰጡ ቦታዎችን ለማስረከብ ለኤርትራ የሚያቀርበው ቅድመ ሁኔታ ኤርትራ በአገሯ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን አሳልፋ እንድትሰጥ ወይም ከአገሯ  እንድታስወጣ የሚጠይቅ መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment