Monday, June 13, 2016

በአልሸባብ የተገደሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥር አሻቀበ

ሰኔ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመከላከያ ምንጮች እንደገለጹት አልሸባብ የተባለው ታጣቂ ቡድን በማእከላዊ ሱማሊያ በኢትዮጵያ የጦር ካምፕ ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት 89 ወታደሮች ሲሞቱ 103 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል። በከባድ ሁኔታ የቆሰሉ ወታደሮች በተከታታይ ቀናት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በጽኑ ከቆሰሉት መካከል ደግሞ 60 ወታደሮች ቅዳሜ ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል ተልከዋል። ቁስለኞቹ በህክምና ላይ መሆናቸውን ኢሳት ከሆስፒታሉ ምንጮች ለማረጋገጥ ችሎአል።

የኢህአዴግ መንግስት በሶማሌ ክልል የሚገኙ የአልሻባብ ታጣቂዎችን ደመሰሰኩ ባለው ሪፖርቱ ፣ በተለያዩ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ገደልኳቸው ያላቸውን ጥቂት አስከሬኖች በማሳየት  ህዝብን ለማሳመን ሙከራ አድርጓል። አልሸባብ ጥቃቱን የፈጸመው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልታዬ ሁኔታ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ተጠቅሞ ሲሆን፣ ይህም በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የኢህአዴግ መንግስት ከ200 በላይ የአልሸባብ ወታደሮችን ገደልኩ ከማለት ውጭ በእርሱ በኩል የሞቱበትን አላስታወቀም። የተገደሉት ወታደሮችም እስካሁን ድረስ ወደ አገራቸው ተመልሰው የክብር አቀባባል አልተደረገላቸውም። ኬንያ፣ ዩጋንዳና ብሩንዲ በአልሸባብ ለተገደሉ ወታደሮቻቸው የክብር ወታደራዊ አቀባባል ማድረጋቸው ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment