Thursday, June 16, 2016

የመንግስት ወታደሮች 400 የኦሮሞ ተወላጆችን መግደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ

ሰኔ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ተካሂዶ በነበረው ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት በገዥው መንግስት ታጣቂዎች ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰላሚዊ ዜጎች በግፍ መገደላቸውንና ከአስር ሺ በላይ መታሰራቸውን ሂውማን ራይትስ ወች ባወጣው ሪፓርት ገልጿል።

ሂውማን ራይትስ ወች ለተወሰደው ኢሰብዓዊ ጨፍጨፋ የኢትዮጵያ መንግስት በአፋጣኝ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብሏል። ገለልተኛ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ በዜጎች ላይ ግድያ፣ እስራትና ከሕግ አግባብ ውጪ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ግለሰቦች ተይዘው ለፍርድ መቅረብ ይገባቸዋል ሲል ጥሪውን አቅርቧል። በ61 ገጽ የምርመራ ሪፓርት ጥናት መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ከአቅም በላይ የታጠቁ ገዳይ ኃይሎችን በማሰማራት በሰላማዊ ዜጎች ላይ አስፈላጊ ያልሆነ የጅምላ ግድያና እስራት አድርሷል። በተጨማሪም በወህኒ ቤት ውስጥ ያሉ እስረኞችን ሰብዓዊ መብታቸውን በመጣስ አላስፈላጊ የሆነ ግፍ መፈጸሙንና በሕዝባዊው ማእበል እንቅስቃሴ ወቅት መረጃዎች እንዳይሰራጩ እገዳ መጣሉን ገልጿል። ሂውማን ራይትስ ወች በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ቁጥራቸው 125 ዜጎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ በኢትዮጵያ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሕጋዊ መብቶች ሕዝባዊ ተቃውሞው ከጀመረበት ከጥቅምት ወር ጀምሮ በፀጥታ ኃይሎች ተከልክለዋል።

በሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ዳሬክተር የሆኑት ሌስሌ ሌፍኮው እንዳሉት የኢትዮጵያ የደኅንነት ኃይሎች ለሰው ልጅ ሕይወት ዋጋ ባለመስጠት ከመቶ በላይ ተማሪዎችን አርሶ አደሮችንና ሌሎች ሰላማዊ ዜጎችን በግፍ ገለዋል። መንግስት በግፍ ያሰራቸውን ሰላማዊ ዜጎች ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች በነጻ ሊለቃቸው ይገባል። በታጣቂዎች ለተፈፀመባቸው በደልም ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል። ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ ግድያውን የፈፀሙት ታጣቂዎች ተለይተው በሕግ ሊጠየቁ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል። የፀጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ ጊዜ በፈፀሙት የጅምላ ግድያ ሰለባ ከሆኑት ሰላማዊ ዜጎች ውስጥ ቁጥራቸው 300 የሚሆኑትን በስምና በምስል የተደገፈ መረጃዎች ሂውማን ራይትስ ወችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጓች ድርጅቶች እጅ ሙሉ መረጃው እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋትን ተከትሎ አነስተኛ እርሻቸው ላይ ያሉትን ነባር ባለይዞታ ድሃ አርሶአደሮችን ከይዞታቸው ያፈናቅላል በማለት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞዋቸውን የገለጹትን ተማሪዎችና አርሶ አደሮች ጨምሮ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በግፍ መገደላቸውን ሪፖርቱ አትቷል። ተቃውሞውን ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ከአስር 10ሽህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች፣ መምህራንን፣ ሙዚቀኞችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፣ የጤና ባለሙያዎችንና ለተማሪዎቹ መጠጊያ የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎችም የጅምላ እስራቱ ሰለባ ሆነዋል። ከተያዙት ውስጥ አብዛኞቹ የተለቀቁ ሲሆን የተወሰኑት ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ መታሰራቸውንና እስካሁን ድረስም ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን፣  በቤተሰባቸው እንደማይጎበኙ፣ ማንኛውንም የሕግ ማማከር አገልግሎት እንደማያገኙ ተደረገዋል።
ዮሴፍ የተባሉ አንድ ነዋሪነታቸው ወለጋ ዞን ውስጥ የሆኑ የ52 ዓመት ጎልማሳ እማኝነታቸውን ሲሰጡ ”እኔ ሕይወቴን ሙሉ የኖርኩት እዚሁ ነው። እንደዚህ ዓይነት እልቂት እስከዛሬ በዓይኔ አይቼ አላውቅም። በፍጹም እንደዚህ ዓይነት የጅምላ ግድያና እስራት በሕዝባችን ላይ ደርሶ አጋጥሞኝም አያውቅም።እያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ አንድ ልጁ ታስሮበታል” ብለዋል።
ታስረው ከተፈቱት ውስጥ ምስክርነታቸው ሲሰጡ በወታደራዊ ካንፖች ውስጥ ተወስደው ሰቆቃ (ቶርቸር) እንደተፈጸመባቸው፣ ሴቶች እንደተደፈሩ እንዲሁም የወሲብ ትንኮሳ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል። በዩንቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የተቀረጸው የቪዲዮ ምስል እንደሚያሳየው ተሰቅለው እንደተደበደቡ ውስጥ እግራቸውን በኤሌትሪክ ንዝረት እንደተቀጡና በብልታቸው ላይ ከባድ ነገር በማሰር ዘግናኝ የሆነ ግፍ እንደተፈጸመባቸው ሪፓርቱ ያትታል።
በኢትዮጵያ ተቀባይነት በሌለው አፋኝ የጸረሽብር ሕግ ሰበብ ካለጥፋታቸው በአሜሪካ ኤንባሲ ፊትለፊት ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ 20 የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ታስረዋል። ተቃውሞውን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች ትምህርት ቤቶችን በመውረር ተማሪዎችን፣ መምህራንን በማሰራቸው ተማሪዎች በፍርሃት የትምህርት ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው የአንደኛ ደረጃ የሁለተኛ ደረጃና የዩንቨርሲቲ ትምህርት መርሃግብሮች ተስተጓጉለዋል። ታጣቂዎች በዩንቨርሲቲ ግቢዎች ውስጥ በመግባት የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ለይተው በተናጠል ጥቃት አድርሰውባቸዋል።
በሕዝባዊ ተቃውሞው ወቅት የውጭ አገር ዜጎች ንብረት መውደማቸውን፣ የመንግስት መስሪያቤቶች መዘረፋቸውንና በእሳት መጋየታቸውንና ከተደረጉት 500 የተቃውሞ ሰልፎች ውስጥ ከ62 በስተቀር ሰላማዊ እንደነበሩም ሪፖርቱ አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝባዊ ነውጡ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ የመረጃ አፈናውን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። በዚህም የፌስቡክና የማኅበራዊ ድረገጾችን ጨምሮ የባህርማዶ የዲያስፓራ ሚዲያዎችን የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሙሉለሙሉ ተዘግተዋል። መንግስት ማስተር ፕላኑን መሰረዙን ቢገልጽም አመጾች ግን ጋብ አላሉም። ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ብዙዎች ታስረዋል፣ ተሰደዋል፣ አድርሻቸው የማይታወቁም አሉ። ለእነዚህ ሁሉ ተመጣጣኝ ያልሆነ ጥቃቶች እስካሁን መንግስት ተጠያቂ ያደረገው አካል አለመኖሩንና ታጣቂዎች አሁንም በዩንቨርሲቲ አካባቢዎች መኖራቸውን ሂውማን ራይት ስዎች አስታውቋል። ከሁለት ዓመት በፊትም በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ተቃውሞዎችን በተመሳሳይ ሁኔታ በኃይል እርምጃ መፈታታቸውንና በወቅቱም አንድም ተጠያቂ አካል እንዳልነበረ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ መንግስት የተወሰዱትን ኢሰብዓዊ የኃይል እርምጃዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ሂውማን ራይት ስዎች፣ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጓች ድርጅቶች በጋራ አውግዘዋል። የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማና የአሜሪካ ሴኔትም በጽኑ ኮንነዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ድርጅትም ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ጉዳዩ እንዲታይና ለምርመራውም ድጋፍን እንደሚያደርግም አስታውቋል።
በኦሮሚያው ክልል ውስጥ የተፈጸመውንን የጅምላ እልቂት ተከትሎ በአብዛሃኛው የውጭ አገራት ለኢትዮጵያ መንግስት ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ አቀዛቅዘዋል። ”ኢትዮጵያ የምትከተለው የእድገት መርህ የዜጎችን ሰብዓዊ መብትን በማፈን የመናገር ነጻነትን በመገደብ፣ በፍትሕ ስም ዜጎች ላይ ሰቆቃ በመፈጸም መሆኑን የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ዳሬክተር የሆኑት ሌስሌ ሌፍኮው አስታውቀዋል።
በቀድሞው የምርጫ ቦርድ ምክትል ሃለፊ በአሁኑ መንግስት የአቋቛመው የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሊ/መንበር አቶ አዲሱ ገብረእግዚአብሄር በኦሮምያ ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝ ነው በማለት ለፓርላማው ሪፖርት ማቅረባቸው ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment