Thursday, June 9, 2016

የአሜሪካ የግብይት ደህንነት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አገሪቱን በጥቁር መዝገብ ላይ ያስቀምጣታል ተባለ

ሰኔ ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአሜሪካ መንግስት የግብይት ደህነት ኮሚሽን ( securities and exchange commission) ባወጣው መግለጫ ፣ የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ለአባይ ግድብ ግንባታ በሚል ከኢትዮጵያውያን ሲሰበስብው የነበረው የቦንድ ሽያጭ ህገወጥ መሆኑን በመጥቀስ አገሪቱ 6 ሚሊዮን 500 ሺ ዶላር  እንድትከፍል መስማማቱን ተከትሎ፣ ውሳኔው የኢትዮጵያን ክብር የሚነካ ብቻ ሳይሆን ፣አገሪቱን በጥቁር መዝገብ ውስጥ blacklist ውስጥ የሚያስገባት መሆኑን በዴንቨር ሜትሮፖሊታን ስቴት ዩኒቨርስቲ እና በዊት ዋተርርስላንድ የአካውንቲንግ ፕሮፌሰሩ ሚንጋ ነጋሽ ገልጸዋል።

ፕ/ር ሚኒንጋ እንዳሉት ድርጊቱ ህግን በመጣስ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን የአገሪቱን ክብር የሚጎዳ እንዲሁም አገሪቱን በጥቁር መዝገብ ውስጥ እንደትገባ የሚያደርግ  ነው። በሌላ በኩል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ባሉበት አሜሪካ 3 ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ብቻ ቦንድ መግዛታቸው መገለጹ፣ ህወሃት በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ለመሰብሰብ ያቀደው እቅድ መክሸፉን ያሳያል ብለዋል። ከአሜሪካ የተሰበሰበው ገንዘብ እጅግ አነስተኛ መሆኑ፣ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የህወሃትን የቦንድ ሽያጭ እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ነው። በአውሮፓና አውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ የወሰደችው እርምጃ በአህጉራቱ ህጎችም ተግባራዊ መሆን ይችሉ እንደሆን በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ አሁንም ገንዘብ ለመሰብሰብ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ወደ አውስትራሊያ መጓዛቸውን ለማወቅ ተችሎአል። የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት ሙክታር ከድር፣ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱና የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብደ ሞሃመድ ኡመር የፌታችን ቅዳሜና እሁድ የተለያዩ ስብሰባዎችን እንደሚያደርጉ ለማወቅ ተችሎአል።

No comments:

Post a Comment