Thursday, June 16, 2016

በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ለመቀልበስ መንግስት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መውሰዱን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አስታወቀ

ኢሳት ዜና (ሰኔ 9 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰውና ከመንፈቅ በላይ በዘለቀው ተቃውሞ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 400 ያህል መሆኑን እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ፣በአስር ሺዎች መታሰራቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) ሃሙስ ይፋ አደረገ። የ314ቱን ሰለባዎች ስም ዝርዝር በቀን እና በአድራሻ በ 86 ገጽ ሪፖርቱ አስፍሯል።
የHuman Rights Watch ሪፖርት ከ125 በላይ የሚሆኑ ምስክሮች፣ የጥቃቱ ሰለባዎች፣ እና የመንግስት ባለስልጣናትን ቃለመጠይቅ ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል። ሰነዱም በኦሮሚያ በተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ማለትም ከህዳር እስከ ግንቦት 2008 ጊዜ ድረስ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።

ጥናቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከህዳር ወር ጀምሮ በአብዛኛው ሰላማዊ በነበሩት ተቃዋሚ ስልፈኞች ላይ ከልክ ያለፈ ሃይል መጠቀሙን በመዘርዘር፣ 400 የሚሆኑ ሰዎችን እንደገለ አብራርቶ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ማቁሰሉንና እንዲሁም በአስር ሺ የሚቆጠሩ ማሰሩን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጠልፎ ወደአልታወቀ ቦታ መውሰዱን ጥናታዊ ሪፖርቱ ያስረዳል።
ለሰው ልጆች የሰብዓዊ መብት መከበር የሚቆረቆረው ይኸው ድርጅት በጥናታዊ ጹሁፉ እንደገለጸው፣ ተቃውሞው ከአዲስ አበባ 80 ኪሎሜርት በምትርቀው ግንጪ ከተማ እኤአ ህዳር 12, 2015 መጀመሩን ገልጿል። የተቃውሞው መነሻም የመንግስት ሃላፊዎች ለኢንቨአስትመት ፕሮጄክትና ለእግር ኳስ መጫወቻ በሚል ሰበብ ጫካ ለመመንጠር በመሞከራቸው እንደሆነ አትቷል። ተቃውሞው በኦሮሚያ ውስጥ ቢያንስ በ17 ዞኖች ውስጥ 400 በሚሆኑ በተለያዩ ቦታዎች ተቀጣጥሎ እንደነበር ሪፖርቱ አመልክቷ።
የአይን ምስሮችን ዋቢ ያደረገው የ Human Rights Watch ጥናት፣ የጸጥታ ሃይሎች ሰብሰብ ብለው ሲጓዙ በነበሩ ሰዎች ላይ ያለልዩነት ተኩሰው ሲገድሉ እንደነበር፣ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ከሰበሰቡ በኋላም የጅምላ ግድያ እንዳደረጉ፣ የታሰሩትንም የማሰቃየት እርምጃ እንደወሰዱባቸው ገልጿል። በኦሮሚያ በመጀመሪያ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ የነበሩት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንደነበር በጥናቱ ላይ ያሰፈረው Human Rights Watch አብዛኞቹ የታሰሩትና የተገደሉት ከ18 አመት በታች የነበሩ ልጆች እንደነበር ገልጿል። የፌዴራል ሃይሎችን ጨምሮ የመንግስት ጸጥታ ሃሎች እና መከላከያ ሰራዊት ያገኟቸውን ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሙዚቀኞ፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ የጤና ሰራተኞች፣ እና እርዳታና መጠለያ ለተማሪዎች የሰጡ ሰዎችን ጭምር እንዳሰሩ በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ እነዚህ እስረኞች ቢለቀቁም፣ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች አሁንም ድረስ ያለምንም ክስ ታስረው እንደሚገኙ፣ የህግ አገልግሎትም ሆነ፣ የቤተሰብ ምክር እንዳላገኙ በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።
ተቃውሞ በተጀመረበት በህዳር 2008 ዓም፣ የተቃውሞው ዋና ትኩረት የፌዴራል መንግስትን ለልማት ያለውን አቀራረብ የሚመለከት እንደነበርና፣ በተለይም የአዲስ አበባን አስተዳደር በተቀናጀ ልማት ከኦሮሚያ ከተሞች ጋር ማስተሳሰር የሚለውን የመንግስት አቋም የኦሮሞን ገበሬዎችን ማፈናቅል የታለመ እንደነበር ሪፖርት ያብራራል። ፕላኑ ገበሬዎችን አባሮ የተወሰኑ የከተማ ሰዎችን ሃብታም ለማድረግ የታለመ ነው በሚል ተቃውሞ እንደቀረበበት ያትታል።
ተቃውሞ እንደቀጠለም፣ በጥር ወር 2008 መጀመሪያ ላይ መንግስት ማስተር ፕላኑ ተሰርዟል በማለት ህዝቡን ለማረጋጋት ሙከራ ማድረጉን የገለጸው የHuman Rights Watch ሪፖርት፣ መንግስት በወሰደው የግድያና የጭካኔ እርምጃ ተቃውሞ እየበረታ መሄዱን ገልጿል። በመሆኑም ገበሬዎችና የማህበረሰብ አባላት የተማሪዎች የነበረውን ተቃውሞ በመቀላቀል የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የባህል ችግሮችን ማንሳታቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።
የHuman Rights Watch ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከህዳር 2008 ጀምሮ የጸጥታ ሃይሎች ከ500 በላይ የሆኑ ሰላማዊ ሰልፎችን ለመበተን ጥይትን ጨምሮ ያልተመጣጠነ ሃይል በሰልፈኞች ላይ መጠቀማቸው በዘገባው ተገልጿል። ተቃውሞ ሲያደርጉ የነበሩና በቃለመጠይቁ የተካተቱ ሰዎች ሲመልሱ የመንግስት የጸጥታ ሃይላት ያለምንም ማስጠንቀቂያ ሰብሰብ ብለው በቆሙ ሰዎች ሳይቀር ያለልዩነት ሲተኩሱ እንደነበር፣ ሌሎች ውሃና የጎማ ጥይት የመሳሰሉ የአድማ ብተና ዘዴዎችን አለመጠቀማቸው ተነግሯል።
የጸጥታ ሃይሎች በእያንዳንዱ ተቃውሞ ብዙ ሰዎችን እንዳሰሩ፣ በሌሊት የቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ ተማሪዎችንና ያስጠለሏቸውን ሰዎችን እንዳሰሩ በሪፖርቱ ተመልክቷል። የጸጥታ ሃይሎች ወሳኝ (ተፅዕኖ አሳዳሪ) ያሏቸውን የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላትን፣ ሙዚቀኞችን፣ መምህራንን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፣ እና ተቃውሞውን ያስተባብራሉ ብለው ያሰቧቸውን ሁሉ ማጎራቸውን የHuman Rights Watch ሪፖርት አስፍሯል።
አብዛኞቹ ታሳሪዎች ከ 18 አመት በታች እንደሆኑ የጠቆመው የHuman Rights Watch ሪፖርት፣ የጽጥታ ሃይሎች ታሳሪዎችን በእስር ላይ እንዳሉ እንዳሰቃዩዋቸው፣ እንዳንገላቷቸው እንዲሁም ሴት እስረኞች በጸጥታ ሃይሎች እንደተደፈሩ ተመልክቷል። አብዛኞቹ እስረኞች በታሰሩበት ወቅት በቂ የምግብ አገልግሎት እንዳልቀረበላቸውም ሪፖርቱ ያስረዳል።
በኦሮሚያ የተካሄደው የመንግስት እርምጃ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ቃለመጠይቅ ተደራጊዎቹ ተናግረዋል። በወለጋ የሚኖሩ የ52 አመቱ አቶ ዮሴፍ እንዳሉት፣ በህይወት ዘመናቸው እንዲህ አይነት ጭቃኔ የተሞላበት ድርጊት እንዳላዩ ገልጸዋል። ተከታታይ እስርና ግድያ እንደተፈጸመና፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ አንድ ወጣት እንደታሰረበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የተቃውሞውን አላማ ለማሳጣት ከህገወጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አገናኝቷል። በመሆኑም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በጸረ-ሽብር ህጉ ከሷቸዋል። አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች 23 ከፍተኛ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አባላት ከአራት ወራት እስር በኋላ በጸረ-ሽብር ህጉ እንደተከሰሱ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል። አቶ በቀለ የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ እንደሆኑ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ፓርቲ በኢትዮጵያ የተጭበረበረ ምርጫ ጭምር እየተሳተፉ የነበሩ ሰው ናቸውም ብሏል።
በአሜሪካ ኤምባሲ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ተማሪዎች በወንጀል ተከሰዋል፣ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ላሉ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የትምህርት አቅርቦትም የጸጥታ ሃይሎች በመገኘታቸው፣ መምህራት በመታሰራቸው እና ተማሪዎች በመታሰራቸው ተማሪዎችም በፍርሃት የተነሳ ወደትምህርት ቤት ባለመምጣታቸው ተስተጓጉሏል ያለው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት፣ ትምህርት ቤቶችም በመንግስት ሃላፊዎች ለሳምንታት እንዲዘጋ ተደርገዋል ሲል አክሎ ገልጿል።
መንግስት ከሁለት አመት በፊት በተወሰደ የሃይል እርምጃ፣ እስርና እና ግድያ የሚመረምር ገለልተኛ አጣሪ ተቋም ማቋቋም አለመቻሉንም ሪፖርቱ በዘገባው አካቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትንም ገድቦ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ያትታል። ባለፈው መጋቢት በኦሮሚያ ክልል የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እንደገደበ፣ ምክንያቱም ፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን (ሶሻል ሚዲያ) ቁልፍ የመረጃ ማስተላለፊያ መንገድ በመሆናቸው እንደሆኑ በመታወቁ እንደሆነ ተጠቅሷል። በውጭ አገር የሚገኙ የሳተላይት ቴሌቪዥን ተቋማት በአገር ቤት እንዳይታዩ አፈና እንደተደረገባቸውና፣ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሳተላይት ዲሾች ተለቅመው እንዲወድሙ እንደተደረገ ሪፖርት አስፍሯል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ክሶች ውድቅ በማድረግ የታሰሩትን እንደፈታ፣ ያልተመጣጠነ ሃይል ለመጠቀሙ ተዓማኒነት ፣ ገለልተኛና ግልጽነት ያለው የምርመራ ኮሚሽን እንዲያቋቁም፣ ያጠፉትን የጸጥታ ሃይሎች እንዳልስፈላጊነቱ አግባብ ባለው የፍርድ ሂደት እንዲቀርቡ ሂዩማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) ጠይቋል።

No comments:

Post a Comment