Monday, June 20, 2016

ሱዳን መከላከያዋን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ማስጠጋቷ ተሰማ

ሰኔ ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ታጣቂ አርሶደአሮች የሱዳንን አርሶደአሮች በማባረር መሬታቸውን እየቀሙ ነው በሚል የአገሪቱ መከላከያ ሃይል የተወሰነ ጦሩን ወደ ድንበር አካባቢ አንቀሳቅሷል። ምንም እንኳ ሱዳን  ወታደሮቿን  ብታንቀሳቅስም፣ እስካሁን ደረስ ወታደሮቿ በኢትዮጵያ አርሶአደሮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ አልደፈሩም።

የሱዳን መንግስት ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ታጣቂ አርሶአደሮች ከ800 ሺ ሄክታር በላይ መሬት ወስደውብናል በማለት ውንጀላ ያቀርባሉ። ፣ የሁለቱ አገራት ድንበር በፍጥነት እንዲካለልላቸውም እየጠየቁ ነው። የኢትዮጵያ አርሶአደሮች በበኩላቸው መሬቱን ለዘመናት ሲጠሙበት መቆየታቸውንና ሱዳኖች በማን አለብኝነት ወስደው እየተጠቀሙበት መሆኑን ይገልጻሉ።  በኢትዮጵያ በኩል መብታቸውን የሚያስከብርልቻው መንግስት እንዳላገኙ በመግለጽም ወቀሳ ያቀርባሉ።  አርሶ አደሮቹ በራሳቸው ተደራጅተው የሱዳን ወታደሮችን ጥቃት ለመመከት እንደሚችሉ በመናገር ላይ ሲሆኑ፣ የሱዳን ወታደሮች ድፍረው ተኩስ የሚከፍቱ ከሆነ ጉዳቱ ይከፋ ይሆናል በማለት ያስጠነቅቃሉ።
በሁለቱ አገር አርሶአደሮች መካከል በየጊዜው ደም አፋሳሽ የሆነ ግጭት ሲካሄድ የቆዬ  ሲሆን፣ አሁን ግን ውጥረቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል። ሱዳኖች በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ በየጊዜው ኢትዮጵያውያን አርሶአደሮችን እያፈኑ ይወስዳሉ። ባለፉት 2 ወራት ብቻ ከ33 ያላነሱ አርሶአደሮች በሱዳኖች ታፍነው ተወስደዋል። ኢንሳ የተባለው የመንግስት የመረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ የሁለቱን አገራትን ድንበር ለማካለል የአየር ላይ ፎቶ ግራፍ ሲያነሳ መክረሙን ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል። ስራው እንደተጠናቀቀም የድንበር ማካለሉ ስራ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

No comments:

Post a Comment