Thursday, June 2, 2016

የህጻናት መንከባከቢያ ጣቢያዎች ቁጥር ከ14ሺ በላይ ደረሰ


ኢሳት ( ግንቦት 25 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች በህጻናት ላይ የሚደርሰው ጉዳት መባባስን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መረጃ ድርጅት የህጻናት መንከባከቢያ ጣቢያዎች ቁጥር ከ 14ሺ በላይ መድረሱን ገለጠ።
በሃገሪቱ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በተለይ በህጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ ያወሳው ድርጅቱ ባለፈው ወር ከአንድ ሺ የሚበልጡ ተጨማሪ የህጻናት የማገገሚያ ጣቢያዎች መቋቋማቸው አስታውቋል።
ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሚሊዮን በላይ ሲሆን ከእነዚሁ ሰዎች መካከል ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸውን የህጻናት መርጃ ድርጅት አክሎ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅትም ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ከምግብ እጥረት የተነሳ የአካልና የጤና ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ያስታወቀው ድርጅቱ አብዛኞቹ ህጻናት በማገገሚያ ጣቢያ እርዳታን የሚፈልጉ እንደሆነ አመልክቷል።
በተለያዩ ክልሎች በዚህ በማገገሚያ ጣቢያ ውስጥ ገብተው ልዩ እንክብካቤ የሚፈልጉ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በቅርቡ 13ሺ አካባቢ የነበረው የጣቢያዎቹ ቁጥር በአሁኑ ወቅት 14ሺ 482 መድረሱን የህጻናት መርጃ ድርጅትቱ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ለተረጂዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ በተገቢው መጠን ባለመገኘቱ ምክንያት ለምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች በቂ አቅርቦት እየተደረገላቸው አለመሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ለድርቁ ድጋፍ የሚያስፈልገው ወደ 1.5 ቢሊዮን አካባቢ መድረሱን ያወሳው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ክፍተት አጋጥሞት እንደሚገኝ በድጋሚ ገልጿል።
ለተረጂዎች የሚያስፈልገው ገንዘብ እስከ ነሃሴ ወር ድረስ የሚገኝ ካልሆነም ድርቁ የከፋ ጉዳትን እያስከተለ እንደሚቀጥል የእርዳታ ድርጅቶች በማሳሰብ ላይ ሲሆኑ በተለይ ህጻናት በድርቁ የከፋ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
መንግስት በበኩሉ የእርዳታ ተቋማቱ የሚሰጡትን ትንበያ በማስተባበል የድርቁን አደጋ ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

No comments:

Post a Comment