Tuesday, June 21, 2016

አየር ሃይል የበረራ ስልጠናውን ሙሉ በሙሉ ወደ ድሬዳዋ አዛወረ

ሰኔ  (አሥራ  ራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት አየር ሃይል በዚህ ሳምንት አዳዲስ በገዛቸው የጦር አውሮፕላኖቹ ድሬዳዋ ላይ ወታደራዊ ልምምድ የሚጀምር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓይለት ስልጠና ( pilot Training base) መቀመጫውን እስከሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ከድሬዳዋ ወደ መቀሌ እንዲያዛውር ትእዛዝ ተላልፎለታል።  አየር ሃይል “ለአገራዊ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት አለባችሁ” በሚል ትእዛዝ አየር መንገዱ የድሬዳዋ የበረራ ማሰልጠኛውን እንዲለቅ ያስገደደ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ  አየር መንገድም በድሬዳዋ የቀሩትን 5 የመለማመጃ አውሮፕላኖች በሳምንቱ መጨረሻ ወደ መቀሌ ያዛውራል።

አየር ሃይል፣  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያደርገው የበረራ ስልጠና የአየር ትራፊክ አፈና ( air traffic jam) ይፈጥራል የሚል ስጋት አድሮበታል። አየር ሀይል በመቀሌ አካባቢ የሚያደርገውን ስልጠና ለምን ወደ ድሬዳዋ ማዛወር እንደፈለገ የታወቀ ነገር የለም።

አየር ሃይሉ አስቸኳይ ትእዛዙን ያስተላለፈው  በቅርቡ ከኤርትራ ጋር የተደረገውን ግጭት ተከትሎ ነው። ኤርትራ በግጭቱ 300 የኢትዮጵያ ወታደሮችን መግደሏን፣ በራሱዋ በኩል ደግሞ 18 ወታደሮቿ ብቻ እንደሞቱባት ገልጻለች።
ሰሞኑን በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር የተካሄደውን ውጊያ ተከትሎ በዝግጅት ላይ በነበሩ ሄሊኮፕተሮች ላይ በደረሰ አደጋ፣ ሶስቱ ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል። አደጋው የተከሰተው በድሬዳዋ አየር ምድብ ሲሆን፣ ለአደጋው መንስዔ ሆነው የተገኙት ሌ/ኮሎኔል ፀጋዘዓብ ካሳ የተባሉ አብራሪ ናቸው። ። ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2008 ዓም በኢትዮጵያ አየር ሃይል የድሬዳዋ ምድብ ውስጥ ሄሊኮፕተርን በመሬት ላይ የማሮጥ ስራ ወይንም ኢንጅን ቴስት ረንአፕ (Engine Test Runup) ሲያደርጉ የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ፀጋዘዓብ ካሳ ሌሎች ሁለት የቆሙ ሄሊኮፕተሮችን በመግጨታቸው ሶስቱም ሄሊኮፕተሮች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። አደጋውን ያደረሱት ሌ/ኮሎኔል ፀጋዓብ ካሳ የህወሃት ታጋይ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግ ካድሬዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን በኤርትራ ያለውን መንግስት እንዲቃወሙ ጥሪ ማስተላለፉ ታውቋል። ሰኔ 23 ሜክሲኮ አደባባይ ላይ በተዘጋጀው ሰልፍ ፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ኤርትራውያን በሙሉ ተገኝተው ጦርነቱን እንዲቃወሙ እንዲሁም የኤርትራን መንግስት እንዲያወግዙ የኢህአዴግ ካድሬዎች እየዞሩ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

No comments:

Post a Comment